መጋቢት ፳፩(ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋሉትእና በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በእስር ላይ የሚገኙት ብርሃኑ ተክለ ያሬድ፣ ፍቅረማሪያም አስማማውና እየሩሳሌም ተስፋው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ፍርድ ችሎት ቀርበው ተጨማሪ የ28 ቀናት ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ችሎት ከመግባታቸው በፊት በፈገግታ በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ የነበሩትን ቤተሰቦቻቸውን፣ ጓደኞቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ሰላም ሲሉ መታየታቸውን ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በፌስ ቡክ ገጹ ዘግቧል።
ጠበቃ ዳዊት ከችሎት በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት መርማሪ ፖሊሶች ምርመራ አለመጨረሳቸውን፣ ተጠርጣሪዎች ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውና ይሄንንም በማጣራት ላይ እንደሚገኙ፣ የቴክኒክ መረጃዎች (የኮምፒውተር፣ የኢንተርኔት፣ የስልክና የፌስ ቡክ) እንደሚቀራቸው፣ ለሽብር ተግባር ብር ሲቀበሉ እና ሲልኩ የነበረውን የባንክ ቤት መረጃ እየተከታተሉ መሆናቸውና ቢለቀቁ መረጃዎችን ሊያጠፉ ስለሚችሉ የተጨማሪ የ28 ቀናት ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ፖሊስም ‹‹የጦር መሳሪያ ተይዟል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በህቡዕ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ከእስር ቢለቀቁ ወደኤርትራ ሰው ወደመመልመል ስራቸው ይመለሳሉ›› የሚል ተቃውሞ በማሰማት፣ የጦር መሳሪያ የታጠቀ የሰው ምስል ለችሎት ማሳየቱንና መሳሪያ የያዘው ግለሰብ ማን እንደሆነ በግልጽ እንደማይታይ ጋዜጠኛ ኤልያስ ዘግቧል።
ፍቅረማርያም እና እየሩሳሌምም ቃላቸውን፣ የፌስ ቡክና ሌሎች መረጃዎችን በምርመራ ወቅት ለፖሊስ መስጠታቸውን፣ መሳሪያ ከተባለው ነገር ጋር የሚያገናኛቸው ነገር አለመኖሩንና ይሄም በግልጽ እንደሚታወቅ በመግለጽ ‹‹መረጃዎች ካሉ ክስ ይመስረትብን ካልሆነ ከእስር እንለቀቅ›› የሚል ሀሳባቸውን ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ከተጠየቀባቸው በኋላ ብርሃኑ ተክለያሬድ ወደ ችሎት መግባቱን፣ መርማሪ ፖሊሱ፣ ብርሃኑ ላይም ‹‹የጦር መሳሪያ ተገኝቷል›› የሚለውን ቃል ሳይደግም በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ያረቀበውን ሀሳብ ለችሎቱ ማስረዳቱን ጠበቃ ዳዊት ተናግረዋል።
ወጣት ብርሃኑ በበኩሉ ‹‹ቃላችንን ለፖሊስና ለፍርድ ቤቱ ሰጥተናል፡፡ የቀረ ነገር የለም፡፡ የእስር ሁኔታችን ከህግ አግባብ ውጪ ነው፡፡ ‹‹ጨለማ ክፍል›› በሚባለው እስር ቤት መብራት 24 ሰዓት ይበራል፡፡፡ እኔ የዓይን ችግር አለብኝ፡፡ በቀን ለ15 ደቂቃ ብቻ ነው ከታሰርኩበት ክፍል ወደ ደጅ የምወጣው፡፡ ቤተሰብና የህግ ጠበቃ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከጠበቃ ጋር ሳልማከር ነው ቃሌን ለፖሊስ የሰጠሁት፡፡ የመብት ጥሰት አለ፡፡ ቤተሰቦቻችንን፣ ጠበቃና ጠያቂዎቻችንን መግኘት ይፈቀድልን፡፡ ሌሎች ከእኔ ጋር የታሰሩ እስረኞች ግን ቤተሰቦቻቸው ሲመጡ ለጥየቃ ይወጣሉ፡፡ በዚህ ላይ ትዕዛዝ ይሰጥበት፡፡ …መረጃዎች ካሉ ክስ ይመስረትብን ካልሆነ ከእስር እንለቀቅ›› ብሏል፡፡
የችሎቱ ሴት ዳኛም የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመው፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብ፣ ከጠበቃ፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ የሚል ትዕዛዝ በቃል ሰጥተው በብርሃኑም ላይ የ28 ቀናት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅደዋል።
No comments:
Post a Comment