መጋቢት ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በአዲስ አበባ በተወሰኑ ክፍሎች የሚገኙ የፌደራል ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ይደግፋሉ በሚል መነሻ ጠንካራ ግምገማ እየተካሄደባቸው ነው።
የፌደራል ፖሊሶች ፌስ ቡክ እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ በተለይ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ይገናኛሉ በሚል የእጅ ስልካቸውን ተነጥቀው ፍተሻ ተደርጎባቸዋል። ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን በተካሄደው ፍተሻ
ቁጥራቸው እስከ 5 የሚደርስ የፌደራል ፖሊስ አባላት ከግንቦት7 እና ኦነግ ጋር በተያያዘ መታሰራቸው ታውቋል። በሁለት የፌደራል ፖሊሶች የሞባይል ስልኮች ላይ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፎቶ ተገኝቶባቸዋል በሚል መታሰራቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ምንጮች እንደሚሉት የአሁኑ ግምገማ 12 የፌደራል ፖሊሶች በተለያዩ ጊዜያት መሳሪያዎቻቸውን ይዘው መጥፋታቸውን ተከትሎ የተካሄደ ነው።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ያለባቸው የስራ ጫናና የሚከፈላቸው ገንዘብ አለመመጣጠን፣ ምንም የትምህርት ደረጃ የሌላቸው ነባር የህወሃት ታጋዮች በተራው የፌደራል ፖሊስ አባል ላይ የሚያደርሱት ጫናና በየጊዜው የሚደረገው አስቸጋሪ ግምገማ ስርአቱን እየተው እንዲሄዱ እንደሚያስገድዳቸው ምንጮች ይገልጻሉ። አብዛኞቹ የፌደራል ፖሊስ አባላት አዛዦች ነባር የህወሃት ታጋዮች ሲሆኑ፣ የሌሎች ብሄር የፖሊስ አባላትን እንደሚንቁና እንደሚያገሉዋቸው የፖሊስ ምንጮች ይገልጻሉ።
No comments:
Post a Comment