የካቲት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃረር ከተማ ካለፈው ሁለት ሳምንት ጀምሮ እንዳዲስ በተጀመረው አፈሳ በርካታ በቀን ስራ የሚተዳዳሩ ነዋሪዎች ታፍሰው ወደ አልታወቀ ስፍራ የተወሰዱ ሲሆን፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ተወስደዋል ብሎዋል።
እሁድ እለት ደግሞ በርካታ አዲስ ምልምል ታዳጊዎች ደግሞ ለወታደራዊ ስልጠና ወደ ብር ሸለቆ ተወስደዋል። እድሜያቸው ከ12 እስከ 13 አመት የሚደርሱ ወጣቶችም ወደ ማሰልጠኛ የተወሰዱ ሲሆን፣ ወላጆች የትውልድ ዘመን ማስረጃ ሰርቲቪኬት ይዘው ቢሄዱም፣ መልስ ሊያገኙ አልቻሉም። ሸንኮር፣ ካናዳ አምባና 17 በሚባሉት አካባቢዎች እናቶች በልጆቻቸው መሄድ ሲያልቀሱ ነበር።
ከጎዳና ላይ እየታፈሱ የተወሰዱት ነዋሪዎች ያለፍላጎታቸው ቢወሰዱም ፣ ሌሎች ግን በወጣው ማስታወቂያ መሰረት መመዝገባቸውን ወኪላችን ገልጿል። ይሁን እንጅ በፈቃደኝነት ተመዘገቡ የተባሉት ብዙዎቹ ታዳጊዎችና እድሜያቸው ከ12 -13 እንደሚሆናቸው ገልጾ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ ለሃዘን ተዳርገዋል። ወጣቶቹ በመከላከያ ውስጥ የተሻለ ትምህርትና የውጭ እድል እንደሚያገኙ ተነግሮአቸው መመዝገባቸውም ወኪላችን አክሎ ገልጿል።
የሃረሪ ክልል ለመከላከያ ሰራዊት የሰው ሃይል አላዋጣም በሚል ከፍተኛ ግምገማ ቀርቦበት ነበር። ያንን ኮታውን ለማሟላት በሚመስል መልኩ እድሜና ፍላጎትን ግምት ውስጥ ሳያስገባ ወጣቶችን ወደ ማሰልጠኛ እንደላከ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘገባውን አጠቃሏል።
ኢሳት በአፋር ክልል በተመሳሳይ መንገድ ወጣቶች ታፍሰው መወሰዳቸውን መዘገቡ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment