- የሄሊኮፕተር እገዛ አልያም የውኃ ቦቴ መኪኖች ድጋፍ እየተጠየቀ ነው
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣ ትላንት ጠዋት የተቀሰቀሰው የእሳት ቃጠሎ አሞራ ገደልበሚባለው አቅጣጫ መዛመቱ ተገለጸ፡፡
በሰሜን በኩል ወንበር ማርያም እየተባለ በሚጠራው የገዳሙ መውጫ ትላንት ጠዋት 2፡00 የተቀሰቀሰው ቃጠሎ፣ በአዱላላ ወረዳ ሠራተኞችና በነዋሪው ሕዝብ ርብርብ ማምሻውን መጥፋቱ ከተገለጸ በኋላ ነው አሞራ ገደል በሚባለው የገዳሙ ደቡባዊ ገጽ በዛሬው ዕለት 5፡00 ላይ ዳግመኛ መቀስቀሱ የተሰማው፡፡
በገዳማውያኑ የጥሩንባ ልፈፋ በተሰባሰበው የገጠሩ ነዋሪና የወረዳው አስተዳደር ሠራተኞች እሳቱን አፈር በማልበስና በቅጠል በመተምተም ለማጥፋት የተቻለ ቢመስልም አንድ የገዳሙ መነኰስ በስልክ እንዳስረዱት፣ ‹‹በደንብ ሳይጠፋ ቀርቶ የታፈነ ነበር፡፡ ዛሬ አሞራ ገደል ጫካ ውስጥ ገብቷል፡፡ ዛፉ እርጥበት አለው፤ ጢሱ ያፍናል፡፡››
ቃጠሎው፣ በአካባቢው ከባድ ነፋስ እየበረታ ከገደሉ ሽቅብና ወደ ጎን ወደ አዱላላ አቅጣጫ የተወሰነ የደኑን ክፍልና እዳሪ መሬት እየበላ በአስጊ ፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡ አኹን ባለው አካሔድ ሳይገታ ወደ ምሥራቅ ከዞረና ጠበል ሜዳውን ካገኘ ወደ ደኑ በጥልቀት ስለሚገባ በእጅጉ አውዳሚ እንደሚኾን የገዳሙ መነኰስ ተናግረዋል፡፡
ከቦታው ገደላማ መልክአ ምድራዊ ገጽታ አንጻር የሚያፍነው ጢስና የቃጠሎው ፍጥነት የመከላከል ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ያስረዱት የገዳሙ መነኰስ፣ አመቺ የሚኾነው አስቸጋሪውን ዐቀበት በመውጣት ለሰው ኃይሉ ውኃ ማቅረብ በሚችሉ መኪኖች አልያም በአየር ርጭትበመኾኑ ከደብረ ዘይት አየር ኃይል የሄሊኮፕተር አልያም የቦቴ መኪኖች እገዛ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኩል እንዲጠየቅ አመልክተዋል፡፡
የትላንቱን ቃጠሎ ለመከላከል በተደረገው ርብርብ ከደብረ ዘይት ከተማ ተጉዘው ሌሊቱን ቃጠሎው በጀመረበት ስፍራው የደረሱ ምእመናንየእሳቱን መስፋፋት የሚገቱ የመከላከል ሥራዎችን ሲሠሩ አድረው መመለሳቸው ተገልጧል፡፡ የከተማው ሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን የወረዳው ማእከል አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እንዲኹም ምእመናን÷ መሬቱን ቆፍሮ በአፈር የመከተር፣ ተቀጣጣይ ጉቶዎችንና ቁጥቋጦዎችን የመመንጠር የመከላከል ሥራ እስከ ንጋት ድረስ ሲሠራ ማደሩ ታውቋል፡፡
ዛሬ ቀትር ላይ መዛመቱ የታወቀውን ቃጠሎ ለማጥፋት ከገዳማውያኑ የድረሱልን ጥሪ መተላለፉን የገለጸ አንድ ምእመን፣ በከተማው በስምንቱም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችና በሠርክ ጉባኤያት ምእመናንንና በጎ አድራጊዎችን በመቅስቀስና በማስተባበር በአፋጣኝ ወደ ስፍራው ለመድረስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡
No comments:
Post a Comment