መጋቢት ፰(ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በአንድ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ተቃውሞ ያገጠማቸው አቶ አብዲ ሙሃመድ ተቃውሞውን ያቀነባበሩት ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የደህንነት ሹሙ ጌታቸው አሰፋ፣ ኢሳት ፣ ግንቦት7 እና የኤራትራ መንግስት በጋራ በመሆን ነው ሲሉ አካራ ኒውስ በተባለው የግል ዌብሳይታቸው ላይ በሶማልኛ ባወጡት ረጅም ጽሁፍ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ተቃውሞውን ሲያሰማ የነበረውን መኮንን የተባለውን ሰው ስም ከፊት በማስቀደም፣ መኮንን ጌታቸው አሰፋ ሃይለማርያም ብለው ጽሁፋቸውን ይጀምሩና ኢሳት ከጀርባ ሆኖ ሲያቀናብር እንደነበር ያትታሉ።
የተቃውሞው እቅድ መክሸፉን የሚገልጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢሳት ቴሌቪዥንም ፕሬዚዳንቱ ሲናገሩት የነበረውን ንግግር ጥሩ ቢሆንም ሆን ብሎ እንዳይተላለፍ ያደረገው፣ እቅዱ መክሸፉን በመረዳቱ ነው ብለዋል።
በወጣው ጽሁፍ ዙሪያ አስተያየቱን የጠየቅነው በአንድ ወቅት የፕሬዚዳንት አብዲ የግል አማካሪ፣ የሶማሊ ክልል ወጣቶች ፕሬዚዳንትና የዚህ ዌብሳይት መስራች የሆነው፣ በአሁኑ ጊዜ በስውዲን አገር በስደት ላይ የሚገኘው ሰብአዊ መብት ተማጓቹ ወጣት አብዱላሂ ሁሴን ፣ አካራ ኒውስ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 በፕሬዚዳንቱ ትእዛዝ መከፈቱንና እርሱ የውብሳይቱ ሃላፊና መስራች ሆኖ መስራቱን ገልጿል። ዌብሳይቱ ለልዩ ሚሊሺያ ከተመደበው የመንግስት በጀት ተቀንሶ መቋቋሙን የሚገልጸው አብዱላሂ፣ በዌብሳይቱ ላይ ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ገንዘብ የሚከፈለውም ከክልሉ ባጀት መሆኑን ይናገራል።
አብዱላሂ ዌብሳይቱን ሲመራ በነበረበት ወቅት ያገኛቸውን ቁልፍ የቪዲዮ ማስረጃዎች በመያዝ ከአገር ከወጣ በሁዋላ፣ ዌብሳይቱ በፕሬዚዳንቱ ታናሽ ወንድም በከድር ሙሃመድ ኡመር ስም እንዲመዘገብ መደረጉን አስረድቷል። በውብሳይቱ ላይ የሚወጣውን ማንኛውንም ጽሁፍ በቃል እየተናገረ የሚያስጽፈው ፕሬዚዳንቱ መሆኑን አብዱላሂ ገልጿል።
አቶ አብዲ፣ የደህንነት ሹሙ አቶ ጌታቸው አሰፋና ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ተቃውሞውን አቀነባብረውታል ብሎ እንደሚያምን የገለጸው አብዱላሂ ምክንያቱ ደግሞ ከወራት በፊት ከተፈጠረው ክፍፍል ጋር ይያያዛል ብሎአል። የክልሉ የምክር ቤት አባላት 7 ለ5 በመወሰን አቶ አብዲን ከስልጣን ለማውረድ ሙከራ ቢያደርጉም፣ አቶ አብዲ ሀረር በሚገኙት በወዳጃቸው በጄኔራል አብራሃ አማካኝነት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ መደረጉን አስታውሷል።
7ቱ የምክር ቤት አባላት አሁንም ተሰደው አዲስ አበባ እንደሚገኙ የሚገልጸው አብዱላሂ፣ በአቶ ሃይለማርያምና በአቶ ጌታቸው አሰፋ እንደሚደገፉም ገልጿል። አቶ አብዲ ለአቶ ሃይለማርያም ከፍተኛ ንቀት ያላቸው ሲሆን፣ ከእርሳቸው የሚመጣውን ትእዛዝ አይቀበሉም። አቶ አብዲ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰላም እንደሆኑ ለማሳየት ሁለቱ ሰዎች ጎን ለጎን ቁጭ ብለው የሚያሳይ ፎርጅድ ፎቶግራፍ አሰርተው በዚሁ ዌብሳይት ላይ እንዲወጣ ካደረጉ በሁዋላ፣ በደረሰባቸው ነቀፋ እንዲነሳ አድርገዋል።
በአቶ አብዲ ጉዳይ በአንድ በኩል የደህንነት ሹሙና አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመከላከያው ሹም ጄኔራል አብርሃ ተፋጠው እንደሚገኙ የሚገልጸው አብዱላሂ፣ እስካሁን ባለው ሂደት መከላከያ በማሸነፉ እነ አቶ ሃይለማርያም ምንም ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል ብሎአል።
ፕሬዚዳንቱ ወደ አገር ሲመለሱ ችግር አይገጥማቸውም ወይ ተብሎ ለተጠየቀው ሲመልስ ደግሞ፣ የመከላከያ ባለስልጣናት እጃው ውስጥ እስካሉ ድረስ ምንም እንደማይሆኑ ይናገራል። ነገሮች ገፍተው ከመጡም ውብሳይቱ የእኔ አይደለም ሊሉ እንደሚችል አክሏል።
በመከላከያ አዛዦችና በአቶ አብዲ መካከል ያለው ግንኙነት ከግል ጥቅም ጋር የተሳሳረ መሆኑንም አብዱላሂ ይናገራል ። አቶ አብዲ ከኦብነግ ጋር የሚደረገው ድርድር ስልጣኔን አደጋ ውስጥ ይጥለዋል በሚል ስጋት አይቀበሉትም።
የአካራ ኒውስ ውብሳይት መተዳዳደሪያ ጽሁፍ እንደሚያሳየው ፣ ዌብሳይቱ ስለሶማሊ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ከባለስልጣኖች አንደበት የሚነገረውን እየተቀበለ እንደሚያሰራጭ ያትታል። በዌብሳይቱ ውስጥ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሚያደርጉዋቸው እንቅስቃሴዎችና የአሜሪካ ጉብኝታቸው በፎቶ ተደግፎ ቀርቧል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ አቶ አብዲ በሚኒሶታ ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሞቻዋል። በተቃውሞው ላይ የሶማሊ ተወላጆች ኢትዮጵአውያንና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሆን አቶ አብዱላሂ እናቶችን የሚገድል፣ ጨፍጫፊ፣ ገዳይ የሚሉ የተቃውሞ ድምጾችን አሰምተዋል
የሶማሊክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ኡመር እና በክልሉ የካቢኔ አባሎች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ተከትሎ በጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት በተካሄደው አስቸኳይ ግምገማ ፣ ፕሬዚዳንቱ ፈጸሟቸው የተባሉ በርካታ ወንጀሎች ተዘርዝረው ቀርበዋል።
ባለፈው ነሃሴ ወር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በሰብሳቢነት በመሩት ግምገማ ላይ ም/ል ጠ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የጠ/ሚኒስትሩ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አለቃ ጸጋየ በርሄ፣የደህንነት ምክትል ሹሙ ኢሳያስ ወጊዮርጊስ ፣የምስራቅ እዝ ዋና አዛዥ ጄኔራል አብርሃ በቅጽል ስማቸው ኳታር ፣ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ሃላፊ ጄ/ል ግርማ የመንጁስ ፣አቶ አዲሱ ለገሰ ፣አቶ አብዲ መሃመድና የተለያዩ የክልሉ የካቢኔ አባላት እንዲሁም ሌሎች 2 የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችም በተገኙበት አቶ አብዲ መገምገማቸውን ኢሳት ዘግቦ ነበር።
አቶ አብዲ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ እሳቸው በሚመሩት ሚሊሺያ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች መገደላቸውን፣በርካታ ሲቪሎች ታስረው ህክምና ሳይገኙ በቀላፎ ፣ በፌርፌርና በሌሎችም እስርቤቶች እንዲሞቱ ማደረጋቸቸውን፣ ከመንግስት የተመደበውን ግዙፍ በጀት ለአንዳንድ የፌደራል ባለስልጣናት በተለይም ለጄ/ል አብርሃ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ ወቅቶች እንዲሰጣቸው በማድረግና በተለያዩ መንገዶች ከፍተኛ ገንዘብ እንዲዘርፍ ማድረጋቸው፣ የአገርሽማግሌዎችን በመሰብሰብ በአንቀጽ 39 መሰረት የራሳችንን መንግስት ስለምናውጅ ለዚህ ታሪካዊ ክስተት ራሳችሁን አዘጋጁ ፣ ፌደራል መንግስትም በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት አይችልም ብለው መናገራቸው ፣ የልዩ ፖሊስ አባላትና የጎሳ አባላሎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲዘርፉ ማሰማራታቸው ፣በክልሉ የሚካሄዱትን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ያለጫራታ በመስጠት ሆን ብለው ለብዝበዛ አዘጋጅተዋል የሚሉ የግምገማ ነጥቦች ቀርበውባቸው ነበር። በግምገማው ወቅት ጄ ል አብርሃ በአቶ አብዲ ላይ የቀረበውን ግምገማ አጥብቀው መቃወማቸው ለአቶ አብዲ የስልጣን እድሜ መራዘም አስተዋጽኦ ማድረጉ በወቅቱ ተዘግቧል።
No comments:
Post a Comment