Tuesday, 24 March 2015

ኢህዴድ በሐረርጌ በጨለንቆ ከተማ ያስገነባው የሰማዕታት ሐውልት የፌዴራል ከፍተኛ ባለስልጣናት ባልተገኙበት መመረቁን ምንጮች ጠቆሙ፡፡

መጋቢት ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅዳሜው የሐውልት ምረቃው ላይ ያልተገኙት ጠ/ሚኒስትሩ፣  በማግስቱ በጅማ ከተማ በተካሄደው የስታዲየም ሰልፍ ላይ ተገኝተው ኦህዴድን የሚያወድስ ንግግር ቢያደርጉም እርሳቸውም ሆኑ የህወሃት ባለስልጣናት በሃውልቱ ምርቃት ላይ አልተገኙም።

የህወሃት ከፍተኛ አዛዦች በሐውልት ምረቃው ላይ ያልተገኙት “ኦህዴድን  የፈጠርነው እኛ ነን” ከሚለው የህወሃቶች ትምክህት ወይም  ኦህዴድ ሰማዕታት አሉኝ በማለት የሚናገረውን ላለመቀበልና ዕውቅና ላለመስጠት ሊሆን እንደሚችል ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
የሐውልት ምረቃው በቴሌቭዥንና በራዲዮ ጭምር በዕለቱ ሽፋን ሳይሰጠው ቀርቶ ሰኞ  በትንሽ የዜና ሽፋን እንዲያገኝ መደረጉን የህወሃት ባለስልጣኖችን አለመደሰት ያሳያል ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል።
በትግራይና በአማራ ክልሎች የሰማአታት ሃውሎቶች ሲመረቁ የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተው መልእክቶችን አስተላልፈው ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኦህዴድ ለኣመታት የተጓተተውን የባህል ማዕከል ረቡዕ ለማስመረቅ አቅዶአል፡፡
አዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ የተገነባው የኦሮሞ የባህል ማዕከል መጠናቀቅ ከነበረበት ከሶስት ዓመት በላይ መዘግየቱን ምንጮች ይገልጻሉ።
የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከሚያገኛቸው ጥቅሞች መካከል ት/ቤቶችን መገንባት፣ የባህል ማዕከላትን  ማቋቋም የሚሉት ጉዳዮች የሚገኝበት ሲሆን በአዲስአበባ በአስሩም ክፍለከተሞች አንድ የኦሮሞ ት/ቤት ለመገንባት ተይዞ የነበረው ዕቅድ ባልታወቀ ምክንያት ሊተገበር አልቻለም፡፡ ኦህዴድ  በህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩ ጥቅሞችን ሆን ብሎ እንዳይፈጸሙ ያደናቅፋል በሚል በራሱ አባላት ጭምር ጠንካራ ትችቶች እንደሚደርስበት ይታወቃል፡፡
በሐረር፣ በጅማ፣ በነቀምቴ፣ በሻሸመኔ፣ በአምቦ፣ በአዳማ ከተሞች በመቶ ሚሊየን ብር ወጪ በማፍሰስ በኣሉን ሲያከብር የቆየው ኦህዴድ ፣ የፊታችን ሐሙስ በሸራተን እና በሚሌኒየም አዳራሽ በሚያካሂደው ፌሽታ በኣሉን ይፈጽማል።
ሕወሃትም  40ኛ ዓመት በአሉን ከመንግስት ካዝና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ  በማውጣት በፌሽታ አክብሮአል።

No comments:

Post a Comment