Thursday, 19 March 2015

በሰሜን ሸዋ የሰማያዊ ዕጩዎች ከፍተኛ ወከባ እየደረሰባቸው ነው


ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia

በሰሜን ሸዋ የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ወከባና የመብት ጥሰት እየደረሰባቸው እንደሆነ በሰሜን ሸዋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የብአዴን ካድሬዎች ፓርቲው ቢሮ እንዳያገኝና የሌላ ሰው ቤት ተከራይተው የሚኖሩት ዕጩዎች የተከራዩትን ቤት እንዲለቁ ቤት ለቤት ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ወ/ሮ ሰርካለም ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡


‹‹አሸባሪዎች ናቸው፡፡ ከቤታችሁ አስወጡ፡፡ እያሉ አከራዮችን ቤት ለቤት እያስፈራሩ ዕጩዎች ቤት እንዲለቁ እያደረጉ ነው›› ያሉት አስተባባሪዋ ቢሮ ለመከራየት ቀብድ ከከፈሉ በኋላ አከራዮቹ ‹‹ቤታችን ድረስ መጥተው አስፈራርተውናል፡፡ ለእናንተ አናከራይም›› እያሉ እንደሚመልሷቸው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች ከስራቸው እንዲፈናቀሉ ወከባ እየደረሰባቸው እንደሆነ የገለጹት አስተባባሪዋ ለአብነት ያህልም አቶ በቀለ ጥላሁንና አቶ አወቀ ይለፋቸው የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በማህበር ተደራጅተው ከዳሸን ቢራ ጋር ለመስራት በሞከሩበት ወቅት የማህበሩ አባላት የሆኑት የብአዴን ካድሬዎች ‹‹እነዚህ የሰማያዊ ፓርቲ ሰዎች ከእኛ ጋር ተደራጅተው መስራት የለባቸውም›› በሚል ከስራቸው እንዲፈናቀሉ አድርገዋል ብለዋል፡፡


በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ የቅስቀሳ ፖስተሮችን ሲለጥፉ የብአዴን ካድሬዎች ፖስተሮችን በመቅደድና ሆን ብለው ላያቸው ላይ ሌሎች ማስታወቂያዎች እንዲለጠፍባቸው በማድረግ ለህዝብ እንዳይደርሱ እያደረጉ እንደሆነ አስተባባሪዋ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment