Wednesday, 4 March 2015

ካህኑ የአረና አባል በመሆናቸው ዘግናኝ ድብደባ ተፈጸመባቸው

የካቲት ፳፭(ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀፍታ ሑመራ ወረዳ በረኸት ከተማ ነዋሪ የሆኑት ቄስ ሕሉፍ ኸሕሳይ የዓረና-መድረክ ኣባል በመሆናቸው ብቻ ዘግናኝ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ከፓርቲው ጽህፈት ቤት የወጣ መረጃ አመለከተ።

እንደ መረጃው ከሆነ ቄስ ህሉፍ በደረሰባቸው ዘግናኝ ድብደባ በህይወትና በሞት መካከል የሚገኙ ሲሆን፤ የተደበደቡበት ምክንያቱ የአረና አባል መሆናቸው ብቻ ነው። የካቲት 17 ቀን 2007ዓመተ ምህረት ምሽት 1፡00 ሰዓት ኣከባቢ በሶስት ታጣቂዎች ከለላነት ተደብቆ የነበረ ሰው በድንጋይ ደጋግሞ በመደብደብ ለከፋ ኣደጋ እንደዳረጋቸው ፓርቲው ጠቅሷል።

ቄስ ህሉፍ መደብደባቸውን ተከትሎ ሰዎች ሊረዷቸው ቢፈልጉም፤ ሶስቱ ታጣቂዎች ሰዎቹ እርዳታእንዳያደርጉላቸው መከልከላቸውን የሚያሳየው መረጃው፤ ታጣቂዎቹ ከዚህም ባሻገር ደብዳቢው በቁጥጥር ስር እንዳይውል ከፍተኛ ከለላ መስጠታቸውን አመልክቷል።
ቄስ ሕሉፍ ኻሕሳይ ባለፈው በክረምት በቀበሌያቸው ህዝብ ፊት እንዲቀርቡ ተደርገው፦ “..ይህ ሰውዬ ዓረና ነው፣ ቤታችሁን እንዳያቃጥልባችሁ! ንብረታችሁን እንዳይሰርቃችሁ..” የሚል ቅስቀሳና የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደተፈጸመባቸው ያወሳው አረና፤ያንንም ተከትሎ ከሌሎች ሶስት የዓረና ኣባላት ጋር ማስፈራሪያና ዛቻ ደርሶባቸው እንደነበር ገልጿል።

በዚህም ሳይበቃ ኣቶ መዓሾ ኣስመላሽ የተባለ የቀበሌው ኣመራር የቤተክርስትያን የሰበካ ጉባዔ አባላትን በመሰብሰብ ፦”…ቄስ ሕሉፍ በዓረናነት ስለተጠረጠረ እንዳይቀድስ ..” የሚል ትእዛዝ ባስተላለፈው መሰረት ከቅዳሴ አገልግሎት መታገዳቸውም ተመልክቷል።

ዘግናኝ ድብደባ የተፈፀመባቸው ከነዚህና ከሌሎች መሰል ውጣ ውረድና ማንገላታት በሁዋላ ነው ያለው አረና-መድረክ፤ <<ህግ ባለበት ሃገር፤ የሰው ልጅ እንዴት እንዲህ ተቀጥቅጦ ይጣላል?” ሲል ጠይቋል።

” ለለውጥ ብለው የተሰዉ 60 ሺ ሰማእታት፣ 100 ሺ ኣካል ጉዳተኞች ውጤታቸው መሆን የነበረበት ይህ ነውን…?” በማለት የጠየቀው ፓርቲው፤ ድርጊቱ በጣም ሗላቀርና ህወሓትን፦ “ታግየ ጣልኩት” ካለው ከደርግ ጋር በእኩልነት የሚያስመድባት ኣፀያፊ ተግባር ነው።” ብሏል።
” በትግራይ የዓረና- መድረክ ኣባል መሆን ይሄ የመሰለ መስዋእትነት ያስከፍላል።” ያለው አረና፤ “አስቃቂ” ያለውን ይህን ተግባር ሁሉም ዜጋ እንዲቃወመው ጥሪ አቅርቧል።

No comments:

Post a Comment