መጋቢት ፲፭(አስራ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በጋራ የፈረሙት አዲሱ ስምምነት ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ በሙሉ ነጻነት የምትሰራውን ስራ እንደሚገድብ ከአረብኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው ሰነድ አመልክቷል።
ሰነዱ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት በምታደርገው ማንኛውም እንቅስቃሴና በየትኛውም የግንባታ ደረጃ ላይ አለማቀፉ አጥኝ ቡድን ለሚሰጠው አስተያየት ተገዢ በመሆን እንድትተገብር ይገልጻል። አጥኝ ኮሚቴው የግድቡ ግንባታ የግብጽንና ሱዳንን የውሃ ድርሻ መጠን ይቀንሳል ወይም በግብጽና ሱዳን አካባቢያዊ ሁኔታ ላይ ተጽአኖ ያመጣል የሚል ድምደማ ላይ ከደረሰ ካሳ እስከመክፈል የሚያደርስ ግዴታም መጣሉ ተመልክቷል።
አጥኚ ቡድኑ የመጨረሻውን የጥናት ውጤት ይፋ ካደረገ በሁዋላ ሶስቱም አገራት እንደሚቀበሉት የተስማሙ ሲሆን፣ ምናልባት አጥኝ ቡድኑ ግድቡ በግብጽና ሱዳን ላይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ያስከትላል ብሎ ቢወስን ኢትዮጵያ የግድቡን ቅርጽ እስከመቀየር ልትደርስ ትችላለች።
ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ፣ ከግብጽና ሱዳን የውሃ ማጠራቀሚያዎችን የሚጎዳ ከሆነም ኢትዮጵያ አገራቱን ፈጥና የማሳወቅና ለውጥ ማድረግ እንደሚኖርባትም ስምምነቱ ይገልጻል።
የስምምነቱ አብዛኛው ክፍል ኢትዮጵያ ስለምትፈጽማቸው ግዴታዎች ትኩረት ያደረገ ነው። ግብጽና ሱዳን ለአባይ ወንዝ የሚያበረክቱት የውሃ ድርሻ ካለመኖሩ አንጻር ስምምነቱ በዋነኝነት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት የሚገድብ ብቻ ሳይሆን፣ የአባይ ግድብ ግንባታ እጣ ፋንታን ከኢትዮጵያ እጅ አውጥቶ በአለማቀፍ አጥኚዎች እጅ እንዲሆን የሚያደርገው ነው በሚል ትችት እየቀረበበት ነው።
ይሁን እንጅ ሶስቱም አገራት ስምምነቱን በማወደስ ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment