Thursday 20 November 2014

ከ400 በላይ ህዝብ የተፈናቀለበት መሬት በሙስና ተቸበቸበ

ኀዳር ፲፩(አስራ አንድቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በደቡብ ወሎ ዞን በኮምቦልቻ ወረዳ ቀበሌ 11 በተለምዶ ጋሪሳ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ይኖሩ የነበሩ 470 ሰዎች ቦታው ለኢንቨስትመንት ይፈለጋል ተብሎ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ እንዲፈናቀሉ ከተደረገ በሁዋላ፣ በካሬ ሜትር 1 ብር ከ46 ሳንቲም መሬታቸው እንዲጨጥ ተደርጓል።

ጉዳዩ የህዝብ መነጋገሪያ ሆኖ ከቆየ በሁዋላ ሰሞኑን ከህዝቡ እየጨመረ የመጣውን ግፊት ተከትሎ በተደረገ ህዝባዊና የካቢኔ አባላት ስብሰባ፣ የወረዳው አዛዦች ከተፈናቃዩ ደሃ ህዝብ የወሰዱትን መሬት በሙስና መቸብቸባቸውን እርስ በርስ እየተገላለጡ ይፋ አድርገዋል።
የወረዳው ላይዘን ኦፊሰር አቶ ሃብቶም የተባሉ ግለሰብ፣ አስተዳዳሪውን አቶ አበራ አበረን በአዲስ አበባና በባህርዳር መሬት ገዝተው ቤት መስራታቸውንና ቡልዶዘሮችን ገዝተው እያከራዩ መሆኑን ሲያጋልጡ፣ ምክትል ከንቲባው ደግሞ በባንክ ሂሳባቸው 8 ሚሊዮን ብር እንደተገኘባቸውና  በተለያዩ አካባቢዎች ቤቶችንመገንባታቸውን አጋልጠዋል። አጋላጩ አቶ ሀብቶምም እራሳቻው በከተማዋ ሁለት ቦታ ገዝተው ቤት መስራታቸውና መቀሌ ላይ ተጨማሪ ቦታ መግዛታቸው በሌሎች ባልደረቦቻቸው ተጋልጧል።
ሶስቱም ባለስልጣኖች ለጊዜው ከስራቸው ቢታገዱም እስካሁን የተወሰደባቸው እርምጃ የለም። አንዳንድ ተፈናቃይ አርሶደአሮች  አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ በማጣታቸው ለስደትና ለረሃብ መዳረጋቸውን ለኢሳት ገልጸዋል ። ሰዎቹ ከስራ ቢሰናበቱም ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረው መስራታቸው አይቀርም የሚል  ጥርጣሬ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ከ100 በላይ አርሶደሮች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አርሶ አደሮቹ የመሬት ዋስትና ወረቀት እንዲሰጣችሁ በነፍስ ወከፍ 4 ሺ 500 ብር ክፈሉ ተብለው የተጠየቁ ቢሆንም፣ እነርሱ ግን እስከዛሬ ግብር እየከፈልን ኖረናል፣ አሁን ተጨማሪ አንከፍልም በማለት ተቃውመዋል። ይህ ተከትሎ መሬታቸውን እየተቀሙ ይዞታቸው ለኢንቨስተር በሚል ሽፋን እየተቸበቸበ ነው። አብዛኞቹ ባለስልጣኖች ከኢንቨስተሮች ጋር አክሲዎን እንዳላቸው የገለጹት መንጮች በአካባቢው የሚታየው ተደጋጋሚ ግጭት ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን  ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment