Sunday 30 November 2014

ምርጫ መሳተፍ በመርዕ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ወይስ ኢህአዴግን ማጀብ? – ከግርማ ሰይፉ ማሩ

November 30,2014

ሰዎች በማንኛውም መንገድ ሸብረክ ሸብረክ የሚሉ ከሆነ መርህ አልባ መሆናቸውን ከማሳየት ውጭ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ባለፈው ሳምነት ፍኖተ ነፃነት ላይ ወጣቱ ፀሃፊ ኢዮኤል ፍስሃ ዳምጤ ለምን እንደምንፈራ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶን ነበር፡፡ የገዢዎቻችን በትር የበረታብን በእነርሱ ጥንካሬ ሳይሆን ከፍርሃት በመጣ ዝምታችን እንደሆነ አስምሮበታል፡፡ መፍትሔውም ከፍርሃት መላቀቅና ዝምታውን ማፍረስ ነው፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ማንሳት የፈለኩት ደግሞ ለምን ሸብረክ ሸብረክ እንደምንል ነው፡፡
ለምንድነው ኮሽ ሲል ደንግጠን ከቆምንበት “መርዕ” ከምንለው አስተሳሰብ የምንሸራተት? እንዲህ ከሆነ ቀድሞውንም መርዕ አልነበረንም ማለት ነው፡፡ መርዕ ብለን የምንይዘው አሰተሳሰብ በእኔ እምነት ለምናደርገው እንቅስቃሴ የማዕዘን ድንጋይ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ መርዕ ሸርተት ስንል ቀጥሎ የምናገኝው ሌላ የተሻለ ማዕዘን የሚሆን ድንጋይ ሳይሆን ድጥ ወይመ ማጥ ነው የሚሆነው፡፡ ብዙዎች መርዕ የሚመስላቸው በአቋራጭ የሚፈልጉትን ግብ የሚያሳካ አጭር መንገድ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይህ አቋራጭ መንገድ ግን ብዙን ጊዜ ወደ ሌላ ውጥንቅጥ ከመውሰድ አልፎ ለስኬት ሲያበቃ አይታይም፡፡
Girma Siefu

ግልፅ ያልሆነ የህይወት ግብ ያለን ሰዎች የምንሄድበትን ስለማናውቅ ሌሎች በሄዱበት ተከትለን እንነጉዳለን፣ ሌሎች ግባቸውን ሲያሳኩ እኛ የበይ ተመልካች መሆናችን አይቀርም፡፡ ግባችን ግልፅ ያለመሆኑ መድረሻችንን ብቻ ሳይሆን መነሻችንንም ስሚያዛባው ከየት ተነስተን የት እንደምንደርስ፣ እንዴት እንደምንደርስ እንዳናውቅ ያደርገናል፡፡ መርዕ ማለት አሁን ካለንብት ቦታ ተነስተን ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ የምንጓዝበት ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአሰተሳሰብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ልክ መሆን ያለበት ነው፡፡ አንድ አንድ ሰዎች የምንፈልገውን ግብ ለማሳካት ማነኛውንም መንገድ መጠቀም ችግር የለውም ይላሉ፡፡ ይህ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው /the end justify the means/ የሚባለው ዓይነት መሆኑ ሲሆን፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች የምንሄድበት መንገድ እንደ ወጤቱ ሁሉ መርዕ ላይ መመስረት አለበት የሚሉ ናቸው /The means is equally important as the end/:: በግሌ የማምነውም የምከተለውም የኋለኛውን አማራጭ ነው፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው የስግብግቦች መንገድ ነው ብዬ በፅኑ ስለማምን፡፡
ሰሞነኛ ወደ ሆነው የምርጫ አጀንዳ እና በመርዕ ላይ የተመሰረተው የአንድነት ፓርቲ ምርጫ እሳተፋለሁ ውሳኔ እንዴት መታየት እንዳለበት በአጭሩ ይህን አቋም ለደገፉም ሆነ ለተቃወሙ ማሰረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንድነት ፓርቲ ስልጣን የሚገኘው በህዝብ ድምፅ ነው የሚል መርዕ አለው፡፡ የህዝብ ድምፅ የሚገኘው ደግሞ በምርጫ ወቅት መራጩ ህዝብ በሚሰጠው ካርድ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በምርጫ የህዝብ ድምፅ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ብዙዎች ምርጫ ለመሳተፍ እኩል ሜዳ ያሰፈልጋል ይላሉ፡፡ ትክክል ነው እኔም አምንበታለሁ፡፡ ሜዳውን ትክክል ከሚያደርገው አንዱ ጉዳይ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ካልሆነ ማለትም ሜዳው ትክክል ካልሆነ ስልጣን በሌላም መንገድ መያዝ ተቀባይነት አለው የሚል መከራከሪያ ለማቅረብም ሰበብ ይሆናል፡፡
ስልጣን በተለያየ መንገድ ለመያዝ እንደሚቻል አማራጭ ማሳየት አንድ ጉዳይ ሆኖ እኛ የመረጥነው ብቻ ልክ ነው ማለትም ተገቢ አይደለም፡፡ በተገኘው መንገድ ለመያዝ መሞከር ግን መርዕ አልባ ያደርገናል፡፡ ሰላማዊ ትግል እከተላለሁ ብሎ በሰላማዊ ትግል መርዕዎች አምናለሁ የሚል ማታ-ማታ ወይም ቅዳሜና-እሁድ በሌላ መንገድ ልሞክር የሚል ከሆነ መርዕ አልባነት ነው፡፡ በእኔ እምነት ችግር ያለው የምርጫ ሜዳ ላይ ከሆነ የምርጫው ሜዳው ለማስተካከል ምን አድርገናል? ከሚለው መነሳት አለበት፡፡ ስልጣን የመያዣው መንግድ ኮሮኮንች በዝቶበታል ማለት ኮሮኮንቹን እንዴት እናሻሽል ወደሚል ሊገፋን ይገባል፡፡
ሁሉም ሰው መረዳት ያለበት ገዢው ፓርቲ የምርጫ ሜዳውን ያጠበበው ወይም ኮሮኮንች እንዲበዛበት ያደረገው አውቆ ነው፡፡ ሜዳው ደግሞ የጠበበን ደግሞ አማራጭ አለን የምንል ፓርቲዎች ነን፡፡ አማርጭ ለማቅረብ እድል ስንነፈግ መጠየቅ ያለብን አንድ መስረታዊ ጥያቄ አማራጭ የተከለከለው ህዝብ ምንም ማድረግ አለበት የሚለው ነው? አማራጭ የሚፈልግ ህዝብ ድንጋይ ወይም ጠብመንጃ ይዞ አማራጭ አትከልክሉን ቢል ነው የሚሻለው ወይስ የምርጫ ካርድ ይዞ? አንድነት የመረጠው መስመር የምርጫ ካርድ ይዞ ቢሆን ይሻላል የሚለውን ነው፡፡ ይህ በምንም ዓይነት ሌሎች የመረጡት መስመር አይሰራም ማለት አይደለም፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭውን እንደ መርዕ የተቀበለ ብዙ ሌላ አማራጭ ሊያስብ፣ ሊተገብር ይችላል፡፡ ችግሩ የእኛ ካልሆነ ብሎ የሌሎችን ምርጫ ለማክበር አለመፈለጉ ላይ ነው፡፡
ETHIOPIA ELECTIONS
በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1997 ከተደረገው ምርጫ ውጭ ህዝቡ በምርጫ እንዲሳተፍ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በተገቢው መልኩና ደረጃ ተቀስቅሶዋል የሚል እምነት የለኝ፡፡ ከ1997 በፊት ምርጫ መወዳድር ወያኔን ማጀብ ነው እያልን ምርጫ የሚወዳደሩትን ብቻ ሳይሆን መራጩንም ተሰፋ እያስቆረጥን ኖረናል፡፡ ይህን ምርጫ የማጣጣል ስትራቴጂያችንን በደንብ የተረዳው ገዢው ፓርቲ የራሱን መራጮችና ተመራጮች እያዘጋጀ ውድድር ሲያድርግ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ህዝቡ በምርጫ ካርዱ ቅሬታውን ሲገልፅ እንደ ነበር የገዢው ፓርቲ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴእታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሠ “የመለስ ትሩፋቶች” በሚለው መፅሃፍ አስነብቦናል፡፡ ስለዚህ የአንድነት ቤተሰቦች ምርጫ እንሳተፋለን ስንል መራጮቻችን እንዲመዘገቡ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ የእኛ መራጮች ሲመዘገቡ፣ ገዢው ፓርቲ የእኔ ብሎ ያስመዘገባቸውም ቢሆኑ እኛን ለመምረጥ እንዲችሉ መሸሸጊያ እንሰጣቸዋለን፡፡
ብዙ ሰው መረዳት ያለበት የምርጫ ቅስቀሳ የሚጀመርበት ወቅት መራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ሳምንት ሲቀረው ነው (በ1997 ቀድሞ የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሮ ነበር)፡፡ ለዚህ ነው ገዢው ፓርቲ ሁል ጊዜ የሚጮሁት ካርድ ያልያዙ ናቸው የሚለው፡፡ ያስመዘገባቸውን ስለሚያውቅ ነው፡፡ የእኛ መራጮች ካርድ ባልያዙበት ሁኔታ የፈለገ አማላይ የሆነ ለሀገር የሚጠቅም አማራጭ ብናቀርብ ለማሸነፍ ያለን እድል አነስተኛ ነው፡፡
ማስተላለፍ የፈለኩት ነጥብ ምርጫ እገባለሁ-አልገባም በሚል ዥዋዝዌ ስንጫወት ደጋፊዎቻችን በመራጭነት ሳይመዘገቡ እንዳይቀሩ በአንድነት በኩል የተወሰደው እርምጃ ትልቅ ፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ የምርጫ ፓርቲ መሆናችን የሚታወቅ ቢሆንም እስከ አሁን በተቃዋሚ ፓርቲዎች መስመር ምርጫ መግባትና አለመግባት በቁርጥ ቀድሞ ስለማይወሰን መራጮች ሁለት ልብ እየሆኑ ከጫወታ ውጭ ሲደረጉ ከርመዋል፡፡ ይህ እንዳይደግም መራጮች እንዲመዘገቡ እና በምርጫው ሙሉ ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ ይህን አቋም መያዝ እጅግ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነበር፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው ያልተመዘገበ ደግሞ አይመርጥም፣ ያልመረጠ ደግሞ ድምፁ እንዲከበር ዘብ ሊቆም አይችለም፡፡ ድምፃችን ይከበር የሚለው እንቅስቃሴ የሚጀምረው ከህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እሰከ ድምፅ ቆጠራ ድረስ ይዘልቃል፡፡
ጎበዝ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል እናደርጋልን ስንል የሰላማዊና ህጋዊ ትግል መርዖዎችን ጠንቅቀን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ በስላማዊ ትግል ዋናው ግብ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ ሲሆን፣ ስልጣን መያዝ የሚፈልግ ፓርቲ የህዝብ ይሁንታ ማግኘት የግድ ይለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በምርጫ የሚገኝ ነው፡፡ ምርጫውን የህዝብ ፖለቲካ ተሳትፎ መለኪያ አድርገን ለመውስድ ቁርጠኞች መሆን የግድ ይለናል፡፡
ቸር ይግጠመን

No comments:

Post a Comment