Tuesday 25 November 2014

የኢህአዴግን የአባልነት ፎርም አንሞላም ያሉ ተማሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

በአዊ ዞን  የኢህአዴግን የአባልነት ፎርም አንሞላም ያሉ ተማሪዎች ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ኀዳር ፲፮(አስራ ስድስትቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :- በአዊ ዞን አንከሻ ወረዳ ውስጥ የሚማሩ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች የኢህአዴግን የአባልነት መሙያ ፎርም ወስደው እንዲመዘገቡ በርእሰ መምህራቸው አማካኝነት ቢጠየቁም፣ ከ700 ያላነሱ ተማሪዎች ድርጊቱን ተቃውመዋል።

ተማሪዎቹ የአባልነት ቅጹን በሁለት ቀናት ውስጥ የማይሞሉ ከሆነ ከትምህርት ቤት እንደሚባረሩና ለፈተናም እንደማይቀርቡ ተነግሯቸዋል። “ከእንግዲህ ኢህአዴግ የሚባል ነገር ማየት አንፈልግም” ያሉት ተማሪዎች ፣ በትምህርት ቤት አስተዳደሪዎች የቀረበላቸውን ውትወታ ውድቅ አድርገዋል።
ምንም እንኳ አንዳንድ ተማሪዎች በስጋት የአባልነት ፎርም ቢሞሉም አብዛኛው ተማሪ ግን ጥሎ መውጣቱን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ አመልክቷል። ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የመኢአድ ምክት ሃለፊ አቶ ዘሪሁን ባንቲ፣ ተማሪዎች በሁለት ቀናት ውስጥ ፎርም የማይሞሉ ከሆነ ከትምህርት ገበታቸው እንደሚባረሩ ገልጸው፣ መንግስት በአቋሙ ከጸና በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው በተቃዋሚዎች ላይ እየደረሰ ያለው መዋከብ መጨመሩን የገለጹት አቶ ዘሪሁን፣ የእርሳቸው ልጅ የተቃዋሚ አባል ልጅ ናት በሚል ሰኞ እለት ከትምህርት ቤት ስትመለስ በአንድ የካደሬ ልጅ ተደብድባ ወደ ህክምና መወሰዱዋን ገልጸዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የወረዳውን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሰካም።
ኢህአዴግ የሁለተኛ እና ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አስገድዶ አባል ለማድረግ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችም የአባልነት ፎርም እንደሚሉ እንቅስቃሴ ጀምሯል። እድሜያቸው ከ12 አመት በታች የሆኑ ተማሪዎች ” ታዳጊ የኢህአዴግ አባል” ተብለው ይመዘገባሉ። ኢህአዴግ በመላ አገሪቱ 6 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ይገልጻል። ይሁን እንጅ አብዛኞቹ ድርጅቱን ለጥቅምና ለህልውና ብለው የሚቀላቀሉ በመሆኑ፣ ለኢህአዴግ ህልውና ስጋት መፍጠራቸውን አቶ አዲሱ ለገሰ ለድርጅቱ አመራሮች በጻፉት ወረቀት ላይ ገልጸዋል። ኢህአዴግ ነባር አባላቱን በሁለተኛ ደረጃና በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለመተካት ቢያስብም አብዛኛው ተማሪ ኢህአዴግን መጥላቱ እቅዱ ሊሳካ እንደማይችል የድርጅቱ አባላት ይናገራሉ። የትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ባዘጋጀው የትምህርት ሰራዊት ግንባታ ወረቅት ላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በኢህአዴግ ላይ ጥላቻ እንዳላቸው ማተቱን መዘገባችን ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment