Saturday 21 March 2015

ወተት ምንድነው?






በዶክተር ታደሰ ብሩ
ክፍል አንድ: ትርጉም
1 ወተት፣ ሰዉን ጨምሮ አጥቢ የሆኑ ፍጡራን ሁሉ ጨቅላዎቻቸውን እየመገቡ የሚያሳድጉበት፤ ተፈጥሮ በእናቶች በኩል ለህፃናት ያዘጋጀችው የተመጣጠነ ምግብ ነው። የቤት እንስሳት ወተት ከህፃናት አልፎ ለአረጋዊያንም የብርታት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። ጨጓራችን ውስጥ አሲድ በዝቶ ሲለበልበን ወተት እፎይታን የሚሰጥ መድሀኒት ነው።

2. ወተት በምስሌዓዊ ትርጉሙ ንጽህናን፣ ደግነትን፣ ርህሩህነትን፣ ምሉዕነትን እና እርካታን ይወክላል።
3. “ወተት” ማለት ”ወቅታዊ ተግባራዊ ትግል“ ማለት ነው።
አገራችን ህወሓት በተሰኘ አሲድ እየተቃጠለች ነው፤ በአስቸኳይ ወተት ትሻለች። ጊዜዓችን፣ እውቀታችን፣ ገንዘባችን ሁሉ ለወተት ዝግጅት ይዋል!!!


ክፍል ሁለት፡
ወተት ቁጥር አንድ 1: እንደራጅ! በያለንበት በምስጢር እንደራጅ። አደራጅ እስኪመጣልን አንጠብቅ።
የወተት ምርት እንዲኖር በርካታ ላሞች ሊኖሩን ግድ ነው። ከዚህም አልፎ ላሞቹን መመገብ፣ መንከባበብና ማለብ ይገባል። የጾም ወቅት በመሆኑ ስለ እጸዋት ወተት ማሰብ ለምትፈልጉም፤ እንደ ላም ወተት ሁሉ የእፀዋትም ወተት ለማግኘትም ከአዝርዕቱ ልማት ጀምሮ መለፋት አለበት። ባጭሩ ወተት ለማግኘት ሥራን ማደራጀት ግድ ነው።
ወቅታዊ ተግባራዊ ትግልም (ወተት) የተቀናጀ ሥራ ይፈልጋል፤ ድርጅት ይሻል። ህወሓት በገሀድ እንዳንደራጅ ያገደን በመሆኑ የምንትማመን አራት፣ አምስት ሰዎች ተሰባብሰን ትንሽ አሀድ (ሕዋስ) እንመሥርት። በ 4 እና 5 ሰዎች የጀመርናት፤ እያንዳንዱ አባል በተራው 4፣ 5 ሰው ካሰባሰበ የስብስባችን ብዛት ወደ ሀያ ያድግልናል። አሁንም አንድ እርከን ብናሳድገው ወደ 100 ይዘልልናል። መቶ ሰው የያዘ የምስጢር ድርጅት ብዙ ነገሮችን አቅዶ መከወን የሚችል ነው።
ድርጅት ኃይል ነው። በድርጅት ጉዳይ ላይ ሶሶስ ነገሮች ላይ አጽንዖት መስጠት ያስፈልጋል።

(1) የአባላት ማንነትነት - ሰው ስንመርጥ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። “በመጀመሪያ ማ ከዚያ ምን” First Who then What እንዲሉ ከማን ጋር ለወተት ሥራ እንተዘጋጁ ወቅት ከሁሉ የሚቀድም ሥራ ነው። 

(2) የዓላማ ግልጽነት - ህወሓትን ከስልጣን አባረን ፍትህ የሰፈነባት ኢትዮጵያን እንድትኖረን እንሻለን። 

(3) ዲሲፕሊን - ሥነሥርዓት ከሌለ ድርጅት የለም። በወተት ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ዲሲፕሊን ነብስ አድን ነው።

ወተት፣ ወተት፣ አሁን ወተት 
ጊዜው የወተት ነው። 
መንገዶች ሁሉ ወደ ወተት ያደርሳሉ። 
መጽሀፎች ሁሉ ስለ ወተት ያብራራሉ። 
ሕዝብ ለወተት ይደራጃል። 
ወተት!!!

ክፍል ሶስት
ወተት ቁጥር ሁለት: ምሬታችን እንዲታወቅ እናድርግ
ህወሓት እየጋተን ያለው እሬት የመረረን መሆኑ የምናሳውቅበት መንገድ ፈልገን በተቀናጀ መንገድ ተግባራዊ እናድርግ። ለዱርዬ አገዛዝ “በጨዋነት መገዛት” እንዳሻህ ፈንጭብኝ ማለት ነው። የኢትዮጵያዊያን ጨዋነት ነው የህወሓት ዱርዬዎችን እንዲህ ያጠገባቸው። ይህ ማብቃት አለበት። ሲመረን መመረን ማለት መቻል አለብን። ምሬታችን መግለጫ መንገዶች አሉ፤ አዳዲስ መንገዶችን ደግሞ መፍጠር እንችላለን።
ለምሳሌ፤
ስለ ልማታቸው፣ ሰላማቸውና መልካም አስተዳደራቸው ሲደሰኩሩ ከንፈሮቻችንን አሹለን ዜሮ መሥራት እንችላለን። በእጆቻችን ዜሮ ማሳየትም ሌላ ዘዴ ነው።
ግራፊቲ - በግድዳዎች፣ በምሰሶዎች፣ በመፀዳጃ ቤቶች፣ በአስፋልት፣ በወረቀት ገንዘቦች፣ በሣንቲሞች ላይ የተቃውሞ ጽሁፎች መፃፍ፤
በዘመቻ መልክ ለጦር ሠራዊት አባላት ደብዳቤ መፃፍና ህሊናው የሚወቅሰው ጉዳይ እንዳይሠራ ማሳሰብ (ካስፈለገ አንድ sample ላዘጋጅ እችላለሁ)፤
ለብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድ አባላት ኢሜላቸውን ፈልጎ ለህወሓት ማደር ምን ያህል አዋራጅ እንደሆነ እንዲረዱት ማሳሰብ። ”ወይ ጥላችሁ ውጡ፤ አሊያም ኢህአዴግ ውስጥ ህወሓትን ግደሉ” ብሎ በግልጽ መምከር፤
ህወሓት ከትግራይ ውጭ ላለው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ለትግራይም የማይበጅ እኩይ መሆኑ እንዲረዱና መላ እንዲፈልጉ ለህወሓት አባላት በግልጽ መፃፍ፣
ጆሮ ጠቢዎችን ማጋለጥ፤ ፎቶዎቻቸውን በሶሻል ሚዲያ ማሰራጨት፤
ህሊና ቢስ ለሆኑ ዳኞች፣ ለሀሳዊያን አቅቢያነ ህግ እና ገራፊ ፓሊሶች እረፍት የሚነሳ መልዕክት መላክ፤ ሊከተል የሚችለውን ማሳወቅ፤
ወደ ተከለከሉ ቦታዎች (ለምሳሌ እስር ቤቶች)ምስጢር ማድረሻነት ውሾችን፣ ድመቶችንና ርግቦችን ማሰልጠንና መጠቀም (ይህ በታዳጊ ወጣቶች በቀላሉ ሊሠራ ይችላል)፤
ወረቀት ጽፎ በፊኛዎች አስሮ መልቀቅ፤
ወዘተ ... ወዘተ ...
ወተት ውጤታማ፣ ተግባራዊና ለማስፈፀም በማይቸግሩ ስልቶች የታገዘ እናደርገዋለን!

No comments:

Post a Comment