Thursday 19 March 2015

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ህወሓት/ኢህአዴግ ነው›› አብርሃ ደስታ

የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ‹ሰጡ›

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ህወሓት/ኢህአዴግ ነው›› አብርሃ ደስታ

‹‹የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው›› የሺዋስ አሰፋ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በተከሰሱበት ድርጊት ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ አመራሮችን ጨምሮ 10 ተከሳሾች ዛሬ መጋቢት 10/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መሰረት ከአንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ጀምሮ፣ ‹‹በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?›› የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ለእያንዳንዳቸው የቀረበላቸው ሲሆን ብዙዎቹ ተከሳሾች ምላሻቸውን በቀጥታ ለመስጠት አለመፈለጋቸውን አሳይተዋል፡፡ 

1ኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ‹‹በአቃቤ ህግ እና በፖሊስ ተቀነባብሮ የቀረበብኝን ክስ በተመለከተ ለክሱ እውቅና ላለመስጠት ምንም አልልም፡፡ በክሱ ላይ አስተያየት በመስጠት ለጸረ-ሽብር አዋጁ እውቅና መስጠት አልፈልግም›› የሚል መልስ በመስጠቱ ፍርድ ቤቱ ክሱን ክዶ ቃል እንደሰጠ አድርጎ መዝግቦታል፡፡ 

2ኛ ተከሳሽ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ ‹‹በክሱ ላይ የተመለከተውን ድርጊት እንዳልፈጸምኩ እንኳን እኔ ከሳሾቼም በደንብ ያውቃሉ፡፡ ከሳሾቼ እኔ ድርጊቱን የመፈጸም ፍላጎቱም ሀሳቡም እንደሌለኝ ያውቃሉ›› ብሏል፡፡ 

3ኛ ተከሳሽ ዳንኤል ሺበሽ ደግሞ፣ ‹‹እኔ ስለ ሽብር የሰማሁት ከአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢላደን እና መለስ ዜናዊ ነው፡፡ እኔ አሸባሪ አይደለሁም፤ ሀሳቡም ሆነ ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ባህሌና እምነቴም አይፈቅድልኝም›› ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

4ኛ ተከሳሽ አብርሃ ደስታ ‹‹አሸባሪ ማለት የፖለቲካም ሆነ ሌላ ዓላማውን ሰላማዊ ዜጎችን በማሸበር ለማስፈጸም የሚሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው አሸባሪ ድርጅት ህወሓት/ኢህአዴግ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የዚህ አሸባሪ ድርጅት ተቃዋሚ ነኝ›› ብሏል፡፡ 

5ኛ ተከሳሽ የሺዋስ አሰፋ በበኩሉ፣ ‹‹በመጀመሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ስለሆነ የምናገረው እንዳታቋርጡኝ አደራ እላለሁ፡፡ ክሱ ቅንብር ነው፡፡ ዳኞችም ህጉ የሰጣቸው ነጻነት አይታይባቸውም፡፡ ይህ 19ኛ ወንጀል ችሎት የጦር ችሎት ነው የሚመስለኝ፡፡ 
ስለሆነም የጦር ችሎት በሚመስል ችሎት እየተንገላታን ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡ የሺዋስ በዳኞች በተደጋጋሚ ንግግሩ እንዲቅረጥ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም ክሱን ክዶ ቃል ሰጥቷል በሚል ተመዝገቦለታል፡፡ 

6ኛ ተከሳሽ ዮናታን ወልዴ፣ ‹‹የተዘጋጀብኝን ክስ ያለፍቃዴ እንድተውን እየተገደድኩ ነው›› ብሏል፡፡ 

7ኛ ተከሳሽ አብርሃም ሰለሞን ደግሞ፣ ‹‹የተቀነባበረ ክስ ላይ ምንም ማለት አይቻልም›› ብሏል፡፡

8ኛ ተከሳሽ ሰለሞን ግርማ፣ ‹‹ነጻ ሰው ነኝ፡፡›› 

9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ ‹‹ባህሉንና ፈጣሪውን ከሚያከብር ማህበረሰብ ወጥቼ አሸባሪ ልሆን አልችልም›› ሲል አስረድቷል፡፡

10ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ ተፈሪ ደግሞ፣ ‹‹ድርጊቱን አልፈጸምኩም›› ብሏል፡፡ 

በአጠቃላይ ተከሳሾች ክሱ ላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ክደው ቃል በመስጠታቸው አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ለግንቦት 13፣ 14፣ 15/2007 ዓ.ም ለተከታታይ 3 ቀናት ምስክር እንዲሰማ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment