Thursday 15 January 2015

ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥራለች

14 01 2015 

ለኢቦላ መከላከል የዘመቱት የበሽታው ተጠቂ ሆነው እየተመለሱ ነው፤

ሴራሊዮን በበጎ ፈቃደኝነት ኢቦላን ለመዋጋት ይሰራ የነበረ ኢትዮጵያዊ የአካባቢ ጤና ባለሙያ አዲስ አበባ የኢቦላ ማግለያ ጣቢያ 
ሕክምና ሲደረግለት ከቆየ በኋላ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል። የጤና ጥበቃ ዛሬ ባወጣው መግለጫ «ግለሰቡ በተደረገለት ምርመራ 
የሞተው በኢቦላ ሳይሆን በጭንቅላት ወባ ነው» ብሏል። መጀመሪያ የግለሰቡን በጭንቅላት ወባ መያዝ ያለማረጋገጫ ያቀረበው 
ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እርስበእርሱ በሚምታታ ሃሳብ «ሆኖም ውጤቱን ለማረጋገጥ የደም ናሙና ወደ አሜሪካ CDC ተቋም 
ልከን ውጤት እየተጠባበቅን ነው ከግለሰቡም ጋር ንክኪ የነበራቸው የቤተሰብ አባላት እና ሌሎች ግለሰቦች ከቤት እንዳይወጡ 
ቁጥጥር እያደረግን ነው» ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።




15 01 2015
ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥራለች

☞ ከ10 በላይ ሰዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ በፖሊስ ታግተዋል

ሴራሊዮን ውስጥ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ህይወቱ ያለፈውና በሽታው ኢቦላ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የደም ናሙናው ወደ ውጭ ለምርመራ የተላከው ኢትዮጵያዊ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የአምቡላንስ ሰራተኛና ከእሱ ጋር ተገናኝተዋል የተባሉ ሌሎች 10 ያህል ሰዎች የሚኖሩበት ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሚገኝ ጊቢ በፖሊስ ተከቦ ነዋሪዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዋል።
ኢሳያስ የተባለና ህይወቱ ያለፈውን ኢትዮጵያዊ በአምቡላንስ ሲያመላልስ የነበር ወጣት ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በተለምዶ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከራይቶ የሚኖር ሲሆን እሱን ጨምሮ ከእሱ ጋር የሚኖሩት እህቱና ባለቤቱ እንዲሁም ተከራይቶ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ከ10 በላይ ሰዎች ከህዝብ እንዳይገናኙ በፖሊስ ታግተዋል። ግቢው በፖሊስ ተከቦ ሰው ከግቢው እንዳይወጣና ወደ ግቢው እንዳይገባ መከልከሉን ተከትሎ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥሯል።
የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሶች ኢሳያስ የተባለው ግለሰብ ሟቹን በአምቡላንስ ሲያመላልስ እንደነበር ከትናንት ጠዋት ጀምረው ቢያረጋግጡም እስከ ትናንት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ ከሰው ጋር እንዳይገናኝ ሳይከለክሉት ቆይተዋል ተብሏል። የአምቡላንስ ሾፌሩ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ ከ20 በላይ ሰዎች የሚኖሩ ቢሆንም 10 ያህሉ ግለሰቦች ብቻ ከግቢ እንዳይወጡ የተከለከሉት ዛሬ ጠዋት ነው ተብሏል። ሆኖም ከግቢው ውጭ ከኢሳያስ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ላይ ምንም አይነት ክትትል ያልተደረገ ሲሆን ግቢው ውስጥ ከሚኖሩት መካከልም በጠዋት በስራና በሌሎች ምክንያች የወጡ ግለሰቦችም ተመልሰው ወደ ግቢ እንዳይገቡ ከመከልከላቸው ውጭ ክትትል እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ታውቋል።

የአምቡላንስ ሾፌሩና ከእሱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉበት ግለሰቦች የሚኖሩበት ግቢ በርከት ባሉ ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች መከበቡን ተከትሎ ስጋት የገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበው ስለ በሽታው እየተወያዩ አስተውለናል። ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም የአንቡላንስ ሾፌሩ ከበርካታ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑ፣ እንዲሁም ግቢው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ከግቢ ውጭ የሚገኙ በመሆኑ በሽታው ከተከሰተ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም አስጊ እንደሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በፖሊስና ደህንነት ከበባ ብቻ አንድ ግቢ ውስጥ ተከሰተ የተባለውን ጉዳይ በአግባቡ መያዝ አለመቻሉን ጠቅሰውም «መንግስት ዝግጅት ሳያደርግ ዜጎችን መላኩ ትክክል አልነበረም።» ሲሉ ተችተዋል።
በፖሊስ ከታገቱት መካከል በስልክ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሰዎች ደህንነቶች «ይህ የአገር ሚስጥር በመሆኑ ለማንም እንዳትናገሩ።» ብለው እንዳስጠነቀቋቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል። ፖሊስና ደህንነቶች ሰው እንዳይወጣና እንዳይገባ በመከልከላቸው እስካሁን ምግብ እንዳልገባላቸውና «የሟቹ የደም ናሙና ነገ እስኪመጣ ድረስ ከግቢ መውጣት አትችሉም። ሌሎች ሰዎችም ወደ ግቢ መግባት አይችሉም፡፡ እስከነገ ለማንም መረጃ ባለመስጠት ተባበሩን።» እንደተባሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ፖሊስ ግቢውን በከበበት ወቅት የግቢው ነዋሪዎች «ችግር ካለ ባለሙያ መጥቶ ያረጋግጥ። ፖሊስ ለምን ያግተናል?» በሚል ከግቢው እንወጣለን በማለታቸው ጭቅጭቅ ተፈጥሮ እንደነበርም የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

15 01 2015
በኢቦላ ስጋት የታገቱት 21 ቀን ሊቆዩ ይችላሉ ተባለ


በኢቦላ በሽታ ስጋት ከቤታቸው እንዳይወጡና እንዳይገቡ በፖሊስ እየተጠበቁ ያሉት የፈረንሳይ ሌጋሲዮን ነዋሪዎች በሽታው እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው እስኪታወቅ ድረስ 21 ቀን ቤታቸው ውስጥ ሊቆዩ እንደሚችሉ ከጤና ጥበቃ ባለስልጣናት እንደተነገራቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ዛሬ ከቀኑ 12 ሰዓት አካባቢ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናት መጥተው የጎበኟቸው ሲሆን በአካባቢ ተሰብስቦ ስለ ጉዳዩ የሚነጋገረውን የአካባቢውን ነዋሪ ፖሊስ ከቦታው በትኗል፡፡
ወደ ግቢው የሚገቡ የህክምና ባለሙያዎችና ባለስልጣናት እንዲሁም ሰዎቹ እንዳይወጡ የሚከታተሉት ፖሊሶችና ደህንነቶች ምንም አይነት ጥንቃቄ እንደማያደርጉ ከቤታቸው እንዳይወጡ የተከለከሉት ሰዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ከቤታቸው እንዳይወጡ የተደረጉት 10 ያህል ሰዎች በተለይ ወደ ውጭ የተላከው የሟቹ የደም ናሙና ሰውየው በኢቦላ እንደሞተ ካመለከተ 21 ቀን ሊቆዩ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ፖሊስ ሳይዛቸው ከቤት የወጡት የግቢው ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን ከህመምተኛው ጋር ግንኙነት ነበረው ከተባለው የአምቡላንስ ሾፌሩ ጋር የተገናኙ ቢሆንም ለ21 ቀን ከቤታቸው ውጭ ሊቆዩ ይችላሉ ተብሏል፡፡

15 01 2015
"ሰበር ዜና
Finote nestanet
---------
የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በተለምዶ ሳራአምፖል በመባል በሚጠራው አካባቢ በሚገኘውና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለኢቦላ ህሙማን ማግለያ በሚል ባደራጀው ጤና ማዕከል ውስጥ ቁጥራቸው ያልታወቀ የኢቦላ ህሙማን ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ እንዲሁም የኢቦላ ምልክት የሚታይበት አንድ ግለሰብ ከማግለያ ጣቢያው እንደተሰወረ የፍኖተ ነፃነት ታማኝ ምንጮች አስታወቁ፡፡ ዝርዝሩን ነገ እናቀርባለን፡፡

No comments:

Post a Comment