Friday 2 January 2015

ምእራባዊያን ኢህአዴግን ከተቃዋሚዎች ጋር ለማቀራረብ ላይ ታች እያሉ ነው

ታኀሳስ ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ችግር እየከፋ መሄዱ ለህዝባዊ አመጽ በር ሊከፍት ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው ምእራባዊያን በአሜሪካ ፊት አውራሪነት በአገር ውስጥና በውጭ ያሉትን ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር ለማቀራረብ እየተሯሯጡ መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገለጹ።

እንደምንጮች ገለጻ በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉት ድርጅቶች ውስጥ አንዳንዶችን በማካተት፣ በውጭ ከሚገኙ ገዢውን መንግስት በሃይል እናንበረክካለን ከሚሉ ወገኖች ጋር ለማቀራረብ አሜሪካውያን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን እያነጋገሩ ሲሆን፣ ኖርዌይ ውይይቱን ለማዘጋጀት እየተንቀሳቀሰች ነው።

ኢህአዴግ  በድርድሩ ላይ ለመገኘት ፈቃደኝነቱን መግለጹ የተነገረ ሲሆን፣ በተቃዋሚዎች በኩል ግን አንዳንዶች ለውይይት ለመቀመጥ ፈቃደኝነታቸውን ሲገለጹ ሌሎች ግን እያንገራገሩ ነው።
ምርጫውን ተከትሎ ህዝባዊ አመጽ ቢነሳ ኢህአዴግ ሊወድቅ ይቻላል የሚል ስጋት የገባቸው ምእራባውያን፣ ምናልባትም ኢህአዴግ ለተቃዋሚዎች የተወሰኑ መቀመጫዎችን በመልቀቅ ውጥረቱ እንዲበርድ ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት ይዘዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከሁለት ምርጫዎች በሁዋላ የኢትዮጵያን ምርጫ እንደማይታዘብ ባስታወቀ ማግስት የተጀመረው  የአሜሪካ እና የኖርዌይ ጥረት ይሳካ አይሳካ ለወደፊቱ የሚታይ ነው። በጉዳዩ ዙሪያ የኖረዌይና የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶችን ለማናገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment