Sunday 25 January 2015

አሁን ካልተነሳን መቼ እንነሳለን

January 23, 2015

ግርማ ካሳ

በአዲስ አበባ፣ በጂንካ፣ በደብረ ማርቆስ ፣ በሸዋ ሮቢት እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች ለመብትና ለነጻነት ሰልፍ ተጠርቷል። የብዙዎቻችን ትእግስትና ዝምታ እንደ ፍርህታ በመቁጠር ጥቂቶች ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው። ምናልባትም በያዙት መሳሪያና ባሏቸው ትቂት ሰራዊቶች ይመኩ ይሆናል። ሆኖም እኛ ግን ሚሊዮኖች ነን !!!! የሚሊዮኖች ኃይል ምን እንደሆነ የምናሳይበት ጊዜ ነው።
ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሙሉ መብት አላቸው። ሰልፍ በመጠራቱ የተጣሰ ሕግ አይኖርም። ሕግ መንግስቱ ይፈቅዳል። በመሆኑም በአገር ቤት ያለን ቀጠሯችንን በአደባባዮቹ እናድርግ። በዉጭ ያለን በመንፈስ፣ በጸሎት፣ በፋይናንስና በሕዝብ ግንኙነት ድጋፍ ፣ አገር ቤት ያሉ ዘመዶቻችን እና ጓደኞቻችን ጋር በመደወል፣ ቴክስት በማድረግ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ እናድርግ።
udj-bahirdar19 BBBBBBB
«ነጻነትን ማንም አይሰጥህም። እኩልነትና ፍትህንም ማንም አይሰጥምህ። ሰው ከሆንክ፣ አንተዉ እራስህ ተቀበለው» ነበር ያሉት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስ። ነጻነትና ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትህ፣ እኩልነትና መልካም አስተዳደር፣ ሌሎች የሚሰጡን ሳይሆን፣ ፈጣሪ በቸርነቱ የለገሰን፣ ደፍረንና ፈቅደን የምንቀበላቸው፣ የኛዉ የሆኑ በረከቶች ናቸው።
ነገር ግን ለአመታት መብታችንና ነጻነታችን፣ በጥቂቶች ተገፎ፣ ሁላችንም በየጓዳችን ስንናደድ፣ ስናማርር፣ ስናዝን፣ ስንራገም፣ ልባችን ሲደማ፣ «እንደዉ ምን ይሻላል? » እየተባባልን ስናወራ ቆይተናል። ለዜጎቿ ሁሉ እኩል የሆነች፣ ሕግ የበላይ የሆነባት፣ ፍትህ የሰፈነባት፣ ሕዝቡ ለመሪዎች ሳይሆን መሪዎች ለሕዝብ የሚንበረክኩባት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት ትልቅ ጉጉት አለን።

ማልኮም ኤክስ እንዳሉት፣ ፍትህንና እኩልነትን እንዲያመጡልን፣ ሌሎችን መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዳችን መንቀሳቀስ ይኖርብናል። በአገር ቤት፣ ሰላማዊ፣ የሰለጠነ የፍቅር ፖለቲካ ላይ ያተኮረ፣ እንቅስቅሴ እየተደረገ ነዉ። እንቅስቅሴዎቹበደብረ ማርቆስ፣ በጂንካ፣ በአዲስ አበባ.. እያለ ይቀጥላል። በአገሪቷ ክልሎች ሁሉ ያለው ሕዝቡ መብቱንና ነጻነቱን እንዲያስከብር ቅስቀሳ ይደረጋል። ለምን ? የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ልትመጣ የምትችለው እኛን ጨምሮ ሕዝቡ ቀን ሲል ብቻ በመሆኑ።
በዉጭ አገር ያለነዉ ፣ አገር ቤት ያለው ሕዝብ አካል ነን። «ምን ተደረገ?» እያልን የምንከታተል ብቻ ሳይሆን፣ የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች አካል መሆን መቻል አለብን።በኢትዮጵያ ወገኖቻችን ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነዉ። በዉጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን፣ ከዚህ በፊት ብዙ ለአገራችን ደክመናል። አሁን ወሳኝ ወቅት ላይ እንዳለን ተረድተን፣ ከዚህ በፊት ካደረግነዉ በላይ ለማድረግ እንነሳ። ትላንት ወድቀን ቆስለን ሊሆን ይችላል። የትላንቱ ጠበሳ ወደፊት እንዳንሄድ ሊያግደን ግን አይገባም። ከወደቅንበትና ከተኛንበት ተነስተን፣ ከቆምንበት ተንቀሳቅሰን፣ ወደፊት በመሄድ መቻል አለብን።
እምነት ያለን በጸሎታችን፣ ገንዘብ ያለን በገንዘባችን፣ ጠቃሚ፣ ትግሉን ወደፊት ሊያስኬዱ የሚችሉ ምክሮችና አስተያየቶች ያሉን፣ ሃሳቦቻችን በማቅረብ፣ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። ይገባናልም።
በዉጭ አገር የሚገኙ ሬዲዮች፣ ቴሌቭዥኖች ፣ ድህረ ገጾች፣ የሲቪክ ማህብራትና በዉጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ድጋፋቸዉን እንዲሰጡንም በአክብሮት ጥሪ አቀርባለሁ።
ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን ! በዚህ ወቅት እኛ ካልተባበረን ማን ? ? ዛሬ ካልሆነ መቼ ?

No comments:

Post a Comment