Thursday 19 February 2015

ከ200 በላይ ዕጩዎች የተሰረዙበት ሰማያዊ ፓርቲ የነጻነት ትግሉን እንደሚገፋት አስታወቀ

የካቲት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተለያዩ  የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ በምርጫ ቦርድ ትዕዛዝ የተሰረዙበት መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ የካቲት 22  ከትብብሩ ፓርቲዎች ጋር በ15 ከተሞች የሚያደርገው የተቃውሞ ሰልፍ  የነጻነት ትግል አካል ነው ብሎአል።

የድርጅቱ ሊ/መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ  እንደገለጹት ሰማያዊ ፓርቲ በመላ አገሪቱ በተለይም በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወላይታ፣ በቤንች ማጅ፣ በምዕ/ጎጃም፣ በሲዳማ፣ በከምባታ፣ በጋሞጎፋ፣ አዲስ አበባ፣ በደቡብ ጎንደርና ጉጅን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ከ200 በላይ ዕጩዎቹ ‹‹ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ታዘናል›› በማለት ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤትና ከክልል ምክር ቤቶች ዕጩ ተወዳዳሪዎቹን መዝገብ ላይ እንዲሰረዙ ተደርጓል።
የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች የቦርዱን ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃናን ለማግኘት ቢጥሩም ‹‹ከከተማ ውጭ ናቸው፡፡ አሁን አታገኟቸውም›› መባላቸውን፣ ፕ/ር መርጋ ግን የህወሓትን 40ኛ አመት ለማክበር መቀሌ መሆናቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል ትክክለኛ  እንደሆነ እንዳስረገጠላቸው፣ ይህን የነጻነት ትግልም አጠናክረው እንደሚቀጥሉና የካቲት 22 ፓርቲያቸው ከትብብሩ ጋር በ15 ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ የሚያደርገው ሰልፍ የዚሁ የነጻነት ትግል አካል እንደሆነ ኢ/ሩ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
የ9 ፓርቲዎች ትብብር የካቲት 22 የጠራው የተቃውሞ ሰልፍን በተመለከተ በመንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ፓርቲው ግን የተቃውሞ ሰልፉን በተያዘለት ቀን እንደሚያካሂድ ቀደም ብሎ  አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment