Friday 20 February 2015

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ማደሪያ እንደ አልቤርጎ እየተከራየ ነው



የካቲት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከ2 ሺ 700 በላይ የተማሪዎች ማደሪያ አልጋዎች ለተመላላሽ ተማሪዎችና ለማይታወቁ ሰዎች እየተከራዩ መሆኑ ታውቓል።

በቅርቡ በአክሱም ከተማ በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማዊ ለውጥ ምክርቤት ጉባዔ ላይ ጉዳዩ በይፋ የተነሳ ሲሆን በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ከ750 በላይ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ከ2ሺ 700 በላይ አልጋዎች በድብቅ ሲከራዩ ቆይተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተመላላሽ ተማሪነታቸው የሚያውቃቸው ተማሪዎችና ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች በወር ለአንድ አልጋ 400 ብር ሒሳብ እየከፈሉ እንደሚጠቀሙባቸው መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መሰረት በወር ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ በሙስና ይበላል።

በውይይቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲው አንዳንድ አመራሮች ነገሩን ክደው የተከራከሩ ቢሆንም በመጨረሻ ግን እውነታውን ለመግለጽ ተገደዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተገኘው የማደሪያ ክፍሎች ቁጥር፤ ማደሪያ የለም ተብለው ከሚመላለሱ ተማሪዎች ቁጥር ጋር ተቀራራቢ ሆኖ መገኘቱም በዚሁ መድረክ ይፋ ሆኖአል፡፡

ይህ ዓይነቱ ሙስና በሌሎችም የመንግስት ዩኒቨርሲዎች ከመለመዱ የተነሳ እንደሕጋዊ አሰራር እየታየ መምጣቱንም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

No comments:

Post a Comment