Tuesday 10 February 2015

አቶ አርከበ እቁባይ መለስ ዜናዊን መግደል ጀምረዋል (ሪፖርታዥ)



አቶ አዲሱ በኢህአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ እንጂ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሉም። አቶ አርከበ ደግሞ በመንግሥት እንጂ በድርጅቱ መዋቅር ውስጥ የሉም። መዋቅር የማያገናኛውቸው ከሆነ ሁለቱን ከአንድ ስብሰባ ምን አስቀመጣቸው? የመከራከሪያቸው ፍሬ ነገርስ ስለምን የመለስ አስተምህሮ ሆነ? የመለስ አስተምህሮ ራዕይና ሌጋሲ የአገሪቱ አቅጣጫ መመሪያ ማስፈራሪያ እየሆነ ዋነኞቹን ባለሥልጣናት ሳይቀር እያከራከረ ይመስላል። ወደታች ወረድ ብለን እንመለከተዋለን።

Arkebe Equbay - Ethiopia

በአንድ የቅርብ ስብሰባ ላይ አቶ አዲሱ ለገሠ አቶ አርከበን ሲነቅፉ “ ቆይ ቆይ አርከበ እኔ እዚህችጋር አንድ ጥያቄ አለችኝ። እስኪ ይሄ ያዘጋጀኸው ዶክመንት ከመለስ አስተምህሮ ጋር እንዴት እንደሚሄድ አስረዳኝ……”


ለማናኛውም አቶ መለስ ዜናዊ ሞልተውን ለሄዱት የውድቀትም ሆነ የእድገት ሰሌዳ፣ ከአንዳቸው እንደርስ ዘንድ ምን ያህል ጊዜ ይቀረናል? በራዕይ የተገለጠላቸውን የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ምልክቱን እናይ ዘንድ ምን ያህል መጓዝ ይኖርብናል? ወይስ ደርሰናል ? ወይስ አቅጣጫውን ስተን ሌላ መንገድ ይዘናል? ከእድገቱ ወይስ ከቁልቁልቱ አፋፍ ላይ ነን? በፈጣኑ እድገታችን ፋፍተን እንደ ጽጌረዳ ፈንድተን እንፈካለን ወይስ እንደ ፈንጂው እንጠፋለን? ወዴት እየሄድን ነው?

በወቅቱ እንደተዘገበው 8ኛው የኢህ አዴግ ጉባዔ የተካሄደው ከመስከረም 5-7/2003 ዓ.ም አዳማ የኦሮምያ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነበር። ጉባዔውን በመምራት ላይ የነበሩት አቶ መለስ፣ የአምስት- ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተደረገው ውይይት በቂ እንደሆነ ገልፀው፣ ‹‹የቀረበውን ሪፖርት መፅደቁን የምትደግፉ፣ ያደረጋችሁትን ባጅ ከፍ አድርጋችሁ አሳዩ›› ሲሉ ጠየቁ። ጉባዔተኛው በሙሉ አንገታቸው ላይ ያንጠለጠሉትን ሰማያዊ የጉባዔ ተሳታፊነት መለያ ወደ ሰማይ ቀሰሩ።
‹‹እቅዱን የምትቃወሙና ድምፅ የማትሰጡ?››
ማንም የለም።
“የአምስት- ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጸድቋል።” አሉ።
አዳራሹ በጭብጨባ ተሞላ።
የአቶ መለስ በዚህ ጉባኤ ባሰሙት ንግግር እንዲህ አሉ

IMG_0683

አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ግን ድርጅታቸው ዛሬ ላይ ቆሞ ሲያየው የአቶ መለስ እቅድ ያለቅጥ የተለጠጠ ነበር። ምክንያቱም አልተሳካም። የማይሳካው ነገርም የታቀደው ሆን ተብሎ ነው። አቶ መለስን ልክ አልነበሩም በማለትና እሳቸውን በማምለክ መካከል በመንገላታት ላይ የሚገኘው ድርጅታቸው በጣም የሚያስቅ መግለጫ ይዞ ወጥቷል። የአቶ መለስን ስህተት እንኳ እንድ ራዕይ አይቶት ከሰማይ ከዋክብትን ከማርገፍ ጋር አመሳስሎታል። በሌላ በኩል ደግሞ አቶ መለስ ከላይ በንግግራቸው “wdnþ× lþb‰L ygbà xK‰¶nT ymSfN«„N xdU tÌqÜmN” እ ያሉትን አደጋ ዛሬ መልሶ የሚያመጣ ወይም ድላቸውን የሚቀለብስ አደጋ በገዛ ጓዶቻቸው መጥቶባቸዋል። በቦንድ ሽያጩ ትላልቅ ኢንደስትሪ ዞኖችን በማቋቋም ስም ትላልቅ የውጭ ኢንቨስተሮችን ጓዶቻቸው ወደ አገር ውስጥ እየጋበዙላቸው ነው። ምክንያቱም አቶ መለስ ያሉት እድገት አልመጣም። አገሪቷ በኢኮኖሚ ቀውስ ተዘፍቃ ከሌሎች ችግሮቿ ጋር አብጣ ልትፈነዳ ሰከንድ የምትቆጥር መስላለች…. በኢህአዲግ አመራሮች መካከል ይቅር እንጂ አቶ መለስም ድርጅታቸውንና አገሪቱን ከማይሆን ነገር ውስጥ ዘፍቀዋት ሄደዋል….

መወቃቀስ መያዛቸው ይሰማል። ቀጣዩ አቅጣጫ ይህ ሊሆን ይገባል አይገባም መባባላቸው እየተሰማ ነው። ክርክሩ ንትርክ ከንትርክም አልፎ የተካረረ መስመር እየያዘ መምጣቱ ይሰማል። ይህ ወደ ፖለቲካው ሽኩቻ አድጎ ወይም ሰበብ ሆኖ እንደ ኤርትራው ጦርነት ክፍፍል ዘመን ኢህአዴጎችን ለሁለት እንዳይከፍላቸው አስግቷል። ወይም አስጎምዥቷል።
በሌላ አነጋገር አቶ መለስ ልክ ነበሩ ወይስ አልነበሩም ይከለሱ ወይስ አይከለሱ የሚል ትርጓሜ እየፈጠረ ይመስላል። የመለስ ራዕይ ወይም አስተምህሮ አራማጆችና አስጠባቂዎች ባንድ በኩል ከላሾችና ምንትስሊብራሎችየተባሉትደግሞ በሌላ በኩል ሆነው ለመወጋገዝ በተጠንቀቅ ሆነዋል። የክፍፍል ዓይነቱ ብዙ ነው። ፓርቲ ውስጥ ያሉትን የመንግሥት ሰዎች በአንድ በኩል መንግሥት ውስጥ የሌሉ የፓርቲ ሰዎችን ደግሞ በሌላ በኩል ማሰለፉም እየተሰማ ነው። ለዚህ ሁሉ የልማትና የትንራንስፎርሜሽን እቅዱ ዋነኛው መነጋገሪያ ወይም የመዋጊያ ሜዳ መስሏል።

ሰበብ ሆኖ የሚያነጋግረው ይሄ የ 5 ዓመት እቅዱ ዋነኛው ይሁን እንጂ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ እያደገ የመጣው መናናቅና ዓይን የሚሞላ ሰው በድርጅቱ አመራር ውስጥ አለመገኘት መሆኑም ይወራል። ሥልጣን የባለ ራዕዮች ስለሆነ የነበረውን ማስቀጠል ወይም አዲስ ራዕይ መውለድ ወቅቱ የጠየቀው ጥያቄ መስሏል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ የመጀመሪያውን እቅድ አፈጻጸምን በመገምገምና በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን አስተቃቀድ ላይ አለመግባባት ደንቅሯል። በዚህ ጽሑፍ የምናየው እነዚህን ይሆናል።

የገዢው ፓርቲ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በየዓመቱ የአገሪቱን አጠቃላይ የፖለቲካና ኢኮኖሚ አቅጣጫና ግብ አስመልክቶ ግምገማ ያደርጋሉ። በተለይ የአምስት ዓመቱን የልማትና የትራንስፎርሜሽን አፈጻጸም ይቃኛሉ። አሁን የአምስት ዓመቱ እቅድ ሰኔ ላይ አልቆ ሁለተኛው የአምስት ዓመት የልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ይፋ መደረግ ይጀምራል። በዚህም መሠረት ከወራት በፊት በጥቅምት 2007/ ኖቨምበር 2014 ላይ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል። በዚሁ ስብሰባ የመጀመሪያውን እቅድ ጉድለቶችና ችግሮች ገምግሞ በሁለተኛው የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መነሻ ማዕቀፍ ላይ ተወያይቶ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ አዟል፡፡ የእቅዱ ዋናው ማጠንጠኛ አቅጣጫ የኢንዱስትሪያላዜሽን ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ እንደሚሆን አስምሮበታል፡፡

ይሄ የኢንደስትሪያላዜሽን ትራንስፎርሜሽን ወይም የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ጉዳይ “ዋነኛ” ሆኖ መውጣቱ በአቶ መለስ ብዙም የማይደገፍ አካሄድ መሆኑና አፈጻጸሙም ላይ ልዩነት መኖሩ ይታወቃል። የትራንስፎርሜሽኑ ምሶሶ ኢንደስትሪ መሆኑ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት ቢኖረውም በኢንደስትሪ ዞን አመሠራረት ፖሊሲ ዙሪያ አሁን ያለው የኢህአዴግ አመራር ለሁለት ተከፍሏል። የኢንዱስትሪ ዞኖቹ የት የት አካባቢ ነው መቋቋም ያለባቸው መጠናቸውና አገልግሎታቸው እንዴት ይሆናል የፋይናንስ ድጋፉንስ ከየት ያገኛሉ በየትኞቹ የምርት ዓይነቶች ላይ ማተኮር አለባቸው እነዚህ ሁሉ ኢህአዴጎቹን ያስማሙ አልሆኑም።

ለምሳሌ አንዳንዶቹ ኢንደስትሪያል ዞን (ፓርክ) ላይ ማተኮር አለብን ባዮች ናቸው። የሆነ አካባቢ ትልቅ ቦታ ተከልሎ የተንጣለለ መሬት ይሰጣል። ገንዘብ ይቀርባል። ባንኩ ታክሱ ሁሉ ነገር እዚያው ይጠናቀቃል። ልክ ሞጆ ላይ ለቻይኖቹ እንደሆነው ትልቅ ኢንደስትሪ ዞን ማለት ነው። እዚህኛው ላይ ጥያቄ የሚያነሱት አመራሮች እንደዚያ ያለ ትልቅ ዞን ሲቋቋም የአገር ባለሀብቶች አቅሙ አይኖራቸውም። እንደዚያ ያለ ካፒታል የሚኖራቸው የውጭ ኩባንያዎች ስለሆኑ አገር ቤት ያለው ባለሀብት እየቀነሰ ይመጣል። ያ ደግሞ እንደ ኬንያና መሰል አገሮች ኢንቨስትመንቱን የሚቆጣጠሩት የውጭ ኢንቨስተሮች ይሆናሉ። ይህ አገሪቱን አሳልፎ ለውጭ ባለሀብቶች የመክፈት ስለሆነ የኒዮ ሊብራሎች አስተሳሰብ ነው። ይህ ከኢህአዴግ መርህ፣ ከመለስ አስተምህሮ ጋር ይቃረናል። ስለዚህ እናንተ ካላሾች በራዦች (ሪቪዥኒስት) ናችሁ…. ባዮች ናቸው።

ከሱ ይልቅ በትንናሽ መንደሮች (ሳተላይት) መካከለኛ ኢንደስትሪ ማቋቋም እንደሚሻል ይከራከራሉ። በየተወሰነው ትናንሽ ከተማ ትናንሽ የጎጆ ኢንደስትሪዎችን ብንቋቁም ይሻላል። ያቺ ለአካባቢው ነዋሪ የሥራ እድል ትፈጥራለች። አካባቢውም ለኢንደስትሪው የሚሆን ግብአት (ጥሬ እቃና የሰው ኃይል) በመስጠት ይደግፋል። ስለዚህ መደጋገፍ ይኖራል፡ ፡ ለትንንሽ መንደሮችና ከተሞች እንዲሁም ለገበሬዎች ትንሽ ትንሽ እየሰጡ ከተሠራ እነሱ እያደጉ ይመጡና በረጅም ጊዜ ሂደት ውስጥ ራሳቸውን ወደ ትላልቅ ኢንደስትሪዎች ማሳደግ ይችላሉ ባዮች ናቸው።

ትራንስፎርሜሽን አብይ ዓላማው ገጠሬን ወደ ከተማ መለወጥ ግብርናን ወደ ኢንደስትሪ መቀየር ኤክስፖርት ላይ የተመሠረተ ምርት በማፍራት የአገሪቱን ገቢና የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል የሚለው ሲናገሩት ቢጣፍጥም አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የአመራርና የአስተዳደር ብቃት በቦታው አልተገኘም። የግል ባለሀብቱም ሚናው በግልጽ አልተመለከተም። አንደኛ ይህንን ህልም ሊደግፍ የሚችለው የግል ባለሀብቱ የፋይናንስ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችልበት የብድርም ሆነ የፋይናንስ ምንጭ የለም። የአገር ውስጥ ባንኮች እንዳይበድሩ በመመሪያ ታስረዋል። እያንዳንዱ ባንክ የሚያበድረውን ብድር 27% ቦንድ እንዲገዛ ይገደዳል። ይህ ማለት ለግል ባለሀብቱ ሊያበድር ከሚችለው ገንዘብ ለቦንዱ ይከፍላል ማለት ነው። ስለዚህ ባንኮች ብዙ ባበደሩ ቁጥር ክፍያቸው እየመጨረ ይሄዳል፡፡ በመካከሉ ባለሀብቱ ገንዘብ አያገኝም። ለዚሁ ተብለው የተቋቋሙት እንደ ልማት ባንክ ያሉት የመንግሥት አበዳሪዎችም ቢሆኑ የባንኩ ኃላፊ ሰሞኑን እንደገለጹት ከሆነ መስፈርቱ ቀላል አይደለም። ለተመረጡ ዘርፎች ያውም ተበዳሪዎች ቢያንስ 30 ከመቶ የማዋጣት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። ከውጭ ባለሀብቶች ይልቅ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ሲስተያይ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከባንኩ ብድር የማግኘት ተጠቃሚነታቸው ከመቶ ፐርሰንት ወደ 75 በመቶ እየወረደ መምጣቱም ተገልጿል። ይህም እያደገ ሄዶ ወደፊት አብዛኛውን የባንኩን ብድር የውጭ ባለሀብቶች ጠቅልለው ሊወስዱ የሚችሉበት አቅጣጫ ይታያል።
ሌሎቹ ደግሞ ሲከራከሩ የፋይናንስ ምንጫችንን ከውጭ ቢሆን አፈላልገን እናገኛለን። ለዚህም መፍትሔ የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮችን አፈላልጎ ማግኘት ነው እንጂ እንዲሁ በር ዘግቶ መቀመጥ አያዋጣንም ባዮች ናቸው። የቦንድ ሽያጩ ነገር የመጣው እዚህጋ ይመስላል።።
meles zenawi

መለስ ቢኖሩ ቦንዱ አይኖርም! መለስ እየሞቱ ነው!


የመለስ ሌጋሲ አስጠባቂዎቹ አመራሮች እነ አቶ በረከት እና አባይ ፀሐዬ ቦንዱን በጥብቅ ተቃውመውታል። የቦንዱ ሽያጭ የፓርቲው ዶክመንት ከሚፈቅደው ውጭ አገሪቱን ለውጭ ኃይሎች በርግዶ መስጠት ነው። ለትላልቅ ፕሮጀክቶቻችን የአገር ውስጥ የፋይናንስ አማራጮችን ገና ተጠቅመንና ፈልገን አልጨረስንም። በኒዮ ሊብራሎች ኃይልና ግፊት ነው እዚህ ውስጥ የገባነው ብለው ያምናሉ። ቦንዱ ከኢህአዴግ እምነት ውጭ የተደረገ ፣ ሁሉንም ነገር ከፍቶ የመስጠት ኢኮኖሚውን ለውጭ ኃይላት የመክፈት የመጀመሪያው ዝንባሌና ምዕራፍ ነው። ነገ መለስ ተሟግቶ ያቆየውን ቴሌ ይሸጥ፣ ባንኮች ለውጭ ባለሀብቶች ባለቤትነት ክፍት ይሆኑ…የሚለው ክርክር ጅማሬ ነው ባዮች ናቸው።

የእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ምሬት ስናይ ምናልባትም ወደፊት “ቦንድና ሉአላዊነት በኢትዮጵያ” የሚል መጽሐፍ በክፍፍል አፈንግጦ በሚወጣ ሌላ ባለሥልጣን እናነብ ይሆናል። ምክንያቱም ጨዋታውና መወነጃጀሉ ሁሉ እንደ ኢትዮ ኤርትራ ወቅት ክፍፍል ከላሽና ተቸካይ መባባልን እያመጣ ነው። ሌሎች ተንበርካኪ ይሏቸው የነበሩ ባለሥልጣናት አሁን ደግሞ በተራቸው ተንበርካኪ የሚባሉበት ሁኔታ የተፈጠረ ይመስላል።

የክፍፍሉን ደረጃ አስገራሚ የሚያደርገው ሌላው ነገር ደግሞ የቦንዱ ሽያጭ ውሳኔ የተወሰነበትና ለህዝብ ይፋ የተደረገበት መንገድ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃ/ማርያም (ከአማካሪያቸው አቶ አርከበ ጋር) ቦንድ ሽያጭ የመግባቱን ውሳኔ ሲወስኑ የኢህአዴግን ሥራ አስፈጻሚ አልተነጋገረበትም። በመጀመሪያ በሚኒስትሮች ም/ቤት ተወሰነ። ከዚያ ወደ ፓርላማ ሄደ። ከፓርላማውም በፓርላማው ጠቅላላ (በአዳራሹ) ሳይሆን በኢኮኖሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ብቻ ነው የታየው።

ይህን የሰሙት የፓርቲው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ተቆጡ። እነ ኃ/ማርያም ሥራ አስፈጻሚውን ሳታስፈቅዱ ለምን ገባችሁበት ተብለው ሲጠየቁ ፍርጥም ያለ ምላሽ ሰጡ። 1ኛ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሊነጋገር የሚገባበት ጉዳይ አይደለም። ሁለተኛ የመንግሥት ሚኒስትሮችና ፓርላማው ተነጋግሮበት ወስኗል። 3ኛ በዚያ ላይ የሚኒስትር ም/ቤት አባላትም ውስጥ ቢሆን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት አሉ። ሁሉም የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚዎች የሚኒስትሮች ም/ቤት አባል ባይሆኑም ከሞላ ጎደል ሁሉም ሚኒስትሮች ግን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት 60 ሲሆኑ የሚንስትሮች ም/ቤት አባላት ደግሞ 30 ናቸው። እዚህ ላይ አቶ ኃ/ማርያም ሥር የተጠለሉ የፓርቲው አንጃዎች (ከአቶ መለስ የተማሩትን) ጨዋታውን በሚገባ አውቀውታል። እንዲያውም ይባስ ብለው እንዴ ምን ማለት ነው? ምንስ ቢሆን እኛን እንዴት አታምኑንም? እዚያ ቦታ ስታስቀምጡን ከድርጅታችን ውጭ እንዴት ልንወስን እንችላለን በማለት ተቆጡ።

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ሆነና እነዚያም እንዲሁ ይተዋወቃሉና ውስጣቸው እያረረ በሉ ላሁኑ ይሁን አሉ። እንደዚህ ዓይነት ነገር ግን ለወደፊቱ መደገም የለበትም ይህ ቀላል ውሳኔ አይደለም የድርጅቱን መርሆ የታላቁ መሪያችንን አስተምህሮ የሚቃቀረን ነው አባሎቻችንን ማረጋጋት ይኖርብናል ዓይነት ነገር ብለው ሂስ አስውጠው እንዳይደገም ማስጠንቃቂያ ሰጡ።

ለዚህም ይመስላል አቶ ሱፍያን ወዲያው አደባባይ ወጡና ስለቦንዱ ስለሶቭሪን ቦንዱ መግለጫ ሰጡ። “ሶቭሪን ቦንድ መሸጥ ማለት የኢኮኖሚ ፖሊሲያችንን ቀይረናል ማለት አይደለም። ለሚቀጥለው ሶስትና አራት ዓመት ሌላ የቦንድ ሽያጭ አናወጣም” ብለው ተናገሩ። እዚህ ላይ ፖሊሲ ስለመቀየር አለመቀየር መናገርን ምን አመጣው? ቦንዱንስ የማይሸጡት ለምንድነው? ያቀርብነው ቦንድ የ1 ቢሊዮን ቢሆንም ያገኘነው ግን 2.5 ቢሊዮን ለመግዛት ፈቃደኛ የሆነ ገበያ ነው። ያህን ያህል ገበያ ካገኙ፣ ቦንዱም ያን ያህል ተፈላጊ ከሆነ፣ ለሚቀጥሉት ዓመታት አንሸጥም ማለትን ምን አመጣው? አይለመደንም እንደማለት ይመስላል።
ይህ ዓይነት ልዩነትና መቀበጣጠር የኖረው ሁሉም መሪያችን ነው ብለው የሚያከበሩት ሰው ባለመኖሩ ነው። ሁሉም የሚያከበሩት መሪ (ግለሰብና) ድርጅት የሌለበት ሁኔታ ነው የሚታየው። አንዱ ላንዱ ያለው አክብሮት ጤነኛ አይመስልም። መጥፎ ስሜትም እያሳደሩ ነው። ይህ ከኢኮኖሚ ወጥቶ የፖለቲካ ጉዳይ የማይሆንበት ምክንያት የለም። እነዚህ ሰዎች ልዩነታቸውን ምን ያህል በሰለጠነ መንገድ ይፈታሉ? ከዚህ ገፍተው የሞትና የሽረት ትንቅንቅ (የሰርቫይቫል) ቢያደርጉና ቢሞክሩ ሁሉም ነገር ሌላ መልክ ይኖረዋል።

እነ አርከበ/ኃይለማይርም የቦንዱን ውሳኔ ለብቻቸው ሲወስኑ ምክንያት ነበራቸው። ለምሳሌ ከአቶ መለስ ራዕይ የተለየው የኢንደስትሪያል ዞኑ ፖሊሲ ጉዳይ ሁለቴ ተጥሏል። ቦንዱን በራሳቸው ከወሰኑ በኋላ ለፓርቲው ማስረዳት የመረጡት በዚህ ምክንያት ነው። ይህንም ብናቀርብ ይጥሉብናል። ሰለዚህ ለራሳችን ለምን አናደርገውም የሚል ብልጠት መኖሩ ተነግሯል። በሌላ በኩል ከአቶ መለስ ራዕይ ጋር በተቸከሉትና በቻልነው ፍጥነት ተጠዳድፈን ካፈጠጠብን ቀውስ እውንጣ በሚሉት አባላት መካከል ፍትጊያ ቢርኖም ችግሩ በአንድና በሁለት የመከፈል ሳይሆን ቢያንስ ወደ ሶስት የሚጠጋ ቡድን መፈጠሩም ይሰማል።

በረከት አዲሱ አባይ ፀሐዬ የመለስ ሌጋሲ እናስጠብቅ ባዮች ሆነው አንድ ቡድን ናቸው። አርከበ ዋነኛው ሆኖ ኃይለማርያም ሱፍያን ተክለወልድና ደብረፅዮን ደግሞ ሌላኛው ቡድን ሲሆኑ የማሻሻያ ለውጥ ያስፈልጋል ባዮች ናቸው። ጄኔራል የተባሉት እነ ሳሞራ የመለስ ራዕይ ከሚለው ውጭ ጉዳዩ ብዙም ስለማይገባቸው አገሪቱን በሥልጣን እያሳደረ ነው የሚባለው ሠራዊታቸው ከማንኛቸው ጋር እንደሚቆም ለመገመት ሳያዳግት አልቀረም። ገና እጅ ያልሰጡት እነወይዘሮ አዜብና ቀሪዎቹ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚዎች ከሠራዊቱ ጋር ማንዣበባቸው ይሰማል።

ይህ ጽሑፍ በዘኢትትዮጵያ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቷል; ርዕሱን ግን እኛ ቀይረነዋል::



No comments:

Post a Comment