Monday 9 February 2015

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እናት ደብዳቤ



ቀን 02/06/2007 ዓ.ም

ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡- የልጄ ተመስገን ደሳለኝን ጉብኝት ይመለከታል

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአብራኬ የወጣ ሁለተኛ ልጄ ነው፡፡ ገና ከህፃንነቱ ጀምሮ ለሰው አሣቢ፣ ሀገር ወዳድና ታታሪ ስለመሆኑ ከእኔ በላይ የሚያውቁት ይመሰክራሉ፡፡ ልጄ ተመስገን ለወገኔ አሰብኩ ባለ በእስር ቤት ያለጎብኚ እየተሰቃየብኝ ይገኛል፡፡ መቼም፣ የእናት ሆድ አያስችልምና እባካችሁ ልጄን ታደጉት፡፡ እባካችሁ ቢያንስ ካለበት እየሄድኩ የልጄን አይን እንዳይ እንዲፈቀድልኝ ተባበሩኝ፡፡ የልጄን ድምጽ ከሠማሁ ይኸዉ አንድ ወር ሞላኝ፡፡ ታናሽ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለወንድሙ ብሎ የቋጠረዉን ምሣ ይዞ ዝዋይ ማረሚያ ቤት ቢሄድም በማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች ተደብድቦ የያዘውን ምግብ እንኳ ሣያደርስ ሜዳ ላይ ተደፍቶ ተመልሷል፡፡ መቼም እናንተም ልጆች ይኖራችኋል፤ ደግሞም የልጅን ነገር ታውቁታላችሁ፡፡ እኔ አሁን በእርጅና ዕድሜዬ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ብቆይም ለትንሽ ጊዜያት ነው፡፡ በዚህች ጊዜ ውስጥ ልጄን እየተመላለስኩ እየጠየኩ፣ ድምፁን እያሰማሁ፣ አይዞህ እያልኩ ብኖር ለእኔ መታደል ነበር፡፡ እባካችሁ እርዱኝ የልጄ ድምጽ ናፈቀኝ፡፡ እሱን መጎብኘት የተከለከለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንኳን እስካሁን አላወቅሁም፡፡ ከወንድሙ ድብደባ በኋላም ጥር 10 ወደ ጠዋት አካባቢ የሄዱት ጓደኞቹ እና ወንድሞቹ ሳያዩት ተመልሰዋል፡፡


ተምዬ ስታመም የሚያስታምመኝ፣ “አይዞሽ እማዬ” የሚለኝ ረዳቴ ነው፡፡ ሌላ ዘመድ የለኝም፡፡ የምተዳደረውም ልጆቼ ለፍተውና ደክመው በሚያመጧት ትንሽ ብር ነው፡፡ ዛሬ ግን ይኸዉ ልጆቼም ወንድማቸውን ለማየት እየተንከራተቱ ነው፡፡

በእናታችሁ ይዣችኋለሁ፤ ከቻላችሁ ልጄ እንዲፈታልኝ እና እኔም ያለችኝን ቀሪ የእድሜ ዘመን አይን አይኑን እያየሁ እንድኖር እንድታደርጉልኝ፤ ይህን ማድረግ ከአቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ካለበት ድረስ እየተመላለስኩ እኔና ሌሎች ልጆቼ እንዲሁም ወገኖቹ እንዲጠይቁት ቢደረግልኝ ስል በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ ልጄን አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ነገር ሲገጥመዉ ሆድ ይብሰዋል፡፡ ቢያንስ እንኳን ቤተሰቦቹን ሲያይ ስለሚፅናና ይኸዉ እንዲፈቀድልኝ እማፀናለሁ፡፡ እኔ ምንም አቅም የሌለኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ሁሉንም ለናንተ ሠጥቻችኋለሁ፡፡ ከእግዚአብሄር ጋር እንደምታስተካክሉልኝ እና እንደገና የልጄን ፊት እንዳይ እንደምታደርጉኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡

እንግዲህ የየካዉ ቅዱስ ሚካኤል ይከተላችሁ፡፡ መቼም የእናትን ሆድ ታውቁታላችሁ፤ የልጅ ነገር አያስችልም፡፡ ሆድም ቶሎ ይሸበራል፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እኔንም ልጆቼንም እርዱን እንላለን፡፡

ግልባጭ
- ለጠ/ሚኒስተር ፅ/ቤት
- የህግና፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ
- ለአፈ-ጉባኤ ፅ/ቤት
- የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ)
- ለእምባ ጠባቂ
- ለአሜሪካ ኢምባሲ
- ለእንግሊዝ ኢምባሲ

ከሰላምታ ጋር

ወ/ሮ ፋናዬ እርዳቸው
_________________________________________________________________________
_________________________________________________

ለጋዘጠኛ ተመስገን ደስአለኝ  አጋርንቶን  በማሳየት በፌስ ቡክ ባለው ገፅና ለሚማለከተው ክፍል ደብዳቤ በማስገባትና  በቻሉት መንገድ ሁሉ ትብብሮትን   ይግለፁ ᎓᎓ የህግ የበላይነት በኢትዮጵያ እንዲከበር የሁላችንም ተሳትፎ ወሳኝ ነው ᎓᎓


ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመናገር ነጻነቱን በመጠቀሙ ብቻ፣ የሶስት አመት እስራት ተፈርዶበት ቤተሰቦቹ ካሉበት 162 ኪሎ ሜትር ርቆ በዝዋይ እስርቤት ከተከረቸመበት እነሆ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ ላለፉት 30 ቀናት ደግሞ በህገ መንግስቱ አንቀጽ ሃያ አንድ የተሰጠው መብት ተጥሶ፤ በቤተሰብም ሆነ በወዳጅ ዘመዶቹ እንዳይጠየቅ ተከልክሏል፤ የምግብና የህክምና አገልግሎትም አያገኝም፡፡
ለቀጣዮቹ አምስት ቀናት በበይነ-መረብ ዘመቻ ቢያንስ ይህንን የማረሚያ ቤቱን እርምጃ እንቃወማለን፤ ሲቀጥልም ጋዜጠኝነት ወንጀል አለመሆኑን እንሰብካለን፡፡ ተመስገን በቤተሰብና በወዳጅ ዘመዶቹ እንዲጠየቅ፣ ምግብ እንዲገባለትና የህክምና አገልግሎት የማግኘት መብቱ እንዲከበር አበክረን ድምጻችንን እናሰማለን፡፡ ተመስገን የታሰረለትን ዓላማና እየከፈለ ያለውን ዋጋ እንዘክራለን!
https://www.facebook.com/pages/Free-Temesgen-Desalegn/147763648696884


No comments:

Post a Comment