Thursday 26 February 2015

ኢትዮጵያ፥ኢትዮጵያዊነት እና አንቀፅ 39 (ክፍል 2)


አንቀፅ 39 ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ቻርተር አንቀፅ 78 ጋር ፊት ለፊት ይጋጫል። ይህ ማለት በአንቀፅ 

39 መሰረት መገንጠል የሚፈልግ ክልል ወይም ህዝብ እንደ ሃገር በተባበሩት መንግስታት እውቅና አይሰጠውም። እውቅና 

ካልተሰጠው ደግሞ ሃገር መሆን አይችልም። በድርቅና እና በድንቁርና የሚሆን ነገር የለም።በቃ! የዓለም አሰራር ይሄው ነው። 

የተመድ አንቀፅ 78 በውጭ ወረራ ቅኝ ግዛት ያልተገዙ ሃገራት አንድነታቸውን ማጠናከር ካልሆነ በቀር ተገንጥለው ሃገር መሆን 

እንደማይችሉ ይደነግጋል። በዚህ አንቀፅ መሰረት ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭ ጠላት ተወረርኩ ብሎ መገንጠል የሚችል ህዝብ 

የለም። ኢሕአዴግ “ችግር የለም፤እኔ እገነጥላችኋለሁ!” ቢልም የተባበሩት መንግስታት እውቅናን አያገኝም።ይህ ማለት በዓለም 

ዓቀፍ ህግ ለሃገር ግንባታ የሚያስፈልጉ ተቋማትን እና መከላከያ ሰራዊት ጨምሮ እንዲኖረው አይፈቀድለትም ማለት ነው።

ይሄን የፃፍኩት በእኔ እድሜ ያሉ ወጣቶች የጎሳ ፖለቲካ ቁማር ማስፈፀሚያ እንዳይሆኑ ለማሳሰብ ነው። የተማሩ የምትሏቸው 

ሰዎች እዚያ ውስጥ የገቡት ከሌላው ነጥለው ለብቻ ሊረግጧችሁ እና እናንተን ከሌላው ጋር ተወዳድሮ በፖለቲካ ማሳመን 

ስለሚያቅታቸው ከሌላው የሚነጥላችሁን እና ለማሳመን ከጎሳ መመሳሰል በቀር ምንም እውቀት የማይጠየቅበትን አካሄድ 

ስለመረጡ ነው። በዚህ መንገድ ፖለቲካን የሚያራምዱት አብዛኞቹ ማለት ይቻላል የተማሩት በምዕራቡ ዓለም ቢሆንም በዚያ 

የነበረውን እና ስለ አንድነት የተደረገውን ጦርነት እንዲሁም ያን በማድረጋቸው ያገኙትን ጥቅም እና ዛሬ ላይ ከሌላው ዓለም 

በተሻለ ሃብታም መሆን የቻሉበትን መንገድ በጎሳ ለመነጠል ለሚፈልጉት ህዝብ አይነግሩትም። ምክንያቱም ይህ ህዝቡን 

ያነቃዋልና ነው። የነቃ ህዝብን ደግሞ እንደ ጭቃ በፈለከው ዓይነት ቅርፅ ባሻህ መንገድ አጠፈጥፈውም። ስለዚህ ይህን ማድረግ 

አይፈልጉም። በጎሳ ፖለቲካ የተረጋጋ ሃገር እና ሰላም እመሰርታለሁ ማለት ፈፅሞ የማይቻል ቢሆንም አንድ ህዝብ የመጨረሻ 

ፍላጎቱ ከሆነና ሌላ አማራጭ ከሌለ በግድ አብረህ ኑር ማለት እንደማይቻልም የታወቀ ነው። ይህን ለማድረግ አንቀፅ 39 

በህገመንግስቱ ኖረ አልኖረ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። በደለኝ በሚለው አካል የመገንጠል ‘መብት’ ተሰጥቶት በበዳዩ 

ፍላጎት ነፃ የወጣ ህዝብ የለም።

የአንድነትም ሆነ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች አንዳንዶቹ ብዬ በጨዋ ደንብ ዲፕሎማሲያዊ ካላደረኩት በቀር አብዛኞቹ ፖለቲከኞች 

ያለውን እውነታ እና የዓለም አሰራር መናገር አይፈልጉም። ይህ በማወቅም ባለማወቅም ሊሆን ይችላል።የሚታየው ግን በሁለቱም 

ወገን የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ የሚያስጠብቅ የተካረረ አካሄድ ነው። ይህ ለሁለቱም የሚጠቅም መንገድ አይደለም ብየ 

አምናለሁ። 

ቤንጃሚን ፍራንክሊን ባንድ ወቅት ለአሜሪካ ህዝብ “ለተኩላ ፖለቲከኞች በግ እንዳትሆን፤ይበሉሃልና!” ብሎ መልክት 

አስተላልፏል። እኛም ከመልክቱ ትምህርት መውሰድ ይኖርብናል። ከስሜት እና ከመፈክር ባሻገር እውነትን እንፈልጋት። 

ለጊዜው ፅሁፌን ከብላታን ጌታ ሎሬት ፀጋየ ገ/መድህን ቀዌሳ ‘ኢትዮጵያዊነት’ ላይ ይህችን ልቆንጥርና ልዝጋው። ፅሁፉ 

እንደሚቀጥል ተስፋ አአደርጋለሁ።

•••የኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ

ወንድምህን መጥላት ሳይሆን፥ራስክን ማወቅ ነው ከስሩ።

ሰው በወንድሙ ሲሳለቅ፥ያው በራሱ እንደ መሳለቅ

ነውና ከቅድመ ታሪክ፥ “አስቀድመህ ራስክን እወቅ”

መባሉ በጥላቻ ዚቅ፥ታውረህ ወንድምክን ስትንቅ

ያው ራስህን ነው የናቅከው፥ከራስህ ጋር ነው ትንቅንቅ

የዘረኝነት በሽታ፥መልሶ ራስክን ስለሚያንቅ

መነሻውን ያላወቀ፥መድረሻ ግቡንም አያውቅ።•••

•••የካም ቤት ክብሯን ሳትለቅ፥ስትማጠቅ ከሌሎች ጋር

ኢትዮጵያዊነት ህብር ሆነ፥ባለብዙ ቀለም አውታር

ካም በሕዋው ጠረፍ ዳሱ፥በእምቅድመ ዓለም አድማሱ

ኦሮሞም፥አማራም፥ትግሬም በኢትዮጵያዊ ኩሩ ቅርሱ

ፅኑ ማተብ ነው መንፈሱ፥መልኮስኮስ አይፈቅድም ነፍሱ።

ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ነው በመናፍቅ የቀን እርካብ

ሊደርሱበት የማይቻል፥በትምክህተኝነት ዛብ

ወይ በጎሳ በላይነት፥በጎጠኝነት ልበ እባብ

የማይሞከር እሴት ነው፥በዘረኛና በጠባብ።•••

•••ይሄ ተለጉሞ መዳህ፥ተጨቁኖ መረጋጋት

አጎብድዶ ለአምባገነን፥እንደ መጋጃ መነዳት

ኢትዮጵያዊነት አይደለም!

ይሄ ሆድ አምላኩ ግሳት፥አጉል ማቀርሻት እንደ አራስ

እንደ ተኮላሸ ጥጃ፥የአምባገነን መዳፍ መላስ

ኢትዮጵያዊነት አይደለም!!!!

@Kidus Mehalu

No comments:

Post a Comment